ቅጣት ሰዎች እንዲያሳዩ የማይፈለግን ባህሪ እንዳያሳዩ ወይም የማሳየት እድላቸውን ዝቅ የሚያደርግ መሳሪያ ነው፡፡ልጆችን በመቅጣት አላስፈላጊ የምንለውን ባህሪ እንዳያሳዩ የማድረግ እድል አለን፡፡ከዚህ ጎን ለጎን ቅጣት ልጆች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖም አለ፡፡ከተለያዩ የጥናት ውጤቶች ላይ ያገኘዋቸውን የቅጣት አሉታዊ ተጽእኖ ከዚህ በታች አቀርብላችኋለው፡፡
1.ቅጣት ልጆችን እልሀኛ እና ሀይለኛ ያደርጋል፡፡ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት በተደጋጋሚ ቅጣት የሚደርስባቸው ልጆች በተደጋጋሚ ከማይቀጡት ልጆች አንጻር ሲታዩ በጣም እልሀኛ የመሆን ባህሪ ይታይባቸዋል፡፡
2.ቅጣት ልጆችን ለአሉታዊ የስነ ልቦና ችግር ይዳርጋል፡፡የተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት በተደጋጋሚ ቅጣት የሚፈጸምባቸው ልጆች ድብርት፣ተስፋ መቁረጥ፣የብቸኝነት ስሜት በመሳሰሉት ነገሮች ከመጠቃታቸው በተጨማሪ ለራሳቸው የሚሰጡት ቦታ የወረደ ይሆናል፡፡
3.በተደጋጋሚ የሚቀጡ ልጆች ቅጣትን የመለማመድ እድል አላቸው፡፡ቅጣት በተደጋጋሚ ለሚቀጡ ልጆች እንደ እለት ተእለት ተግባራቸው የመቆጠር እድል አለው፡፡
4.ቅጣት ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አያመጣም፡፡ልጆች በተደጋጋሚ በሚቀጡበት ጊዜ አታድርጉ የተባሉትን ነገር ላያደርጉ ይችሉ ይሆናል፡፡ነገር ግን ያደረጉት ድርጊት ትክክል አለመሆኑን አምነውበት ስላልተዉት ተደብቀው ድርጊቱን የመፈጸም እድል አላቸው፡፡
5.ቅጣት ልጆች ለወላጆቻቸው ጥላቻ እንዲኖራቸው የማድረግ አቅም አለው፡፡ በተደጋጋሚ የሚቀጡ ልጆች ወላጆቻቸውን መፍራት እና መሸሽ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ከወላጅ የሚደብቁት ብዙ ሚሰጥር ይኖራቸዋል፡፡ይህም የልጆችን በቀላሉ ለአቻ ግፊት ሊያጋልጣቸዉ ይችላል፡፡
6.የተለያዩ የጥናት ውጤቶች እነደሚያሳዩት ከሆነ በተደጋጋሚ አካላዊ ቅጣት የሚደርስባቸው ልጆች አእምሮአዊ እና ሀይለ ስሜታዊ እድገት ውስንነት ይታይባቸዋል፡፡
ቅጣትን እንዴት ብንጠቀመው ውጤታማ ያደርጋል?
======
ቅጣት በተለይ አካላዊ ቅጣት ልጆች ላይ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ያደርሳል፡፡ሌላ አማራጭ ካላጣን በስተቀር ባንጠቀመው ይመረጠል፤ ከተጠቀምነው ግን ከግንዛቤ ልናስገባቸው የሚገቡ የተወስኑ ነጥቦችን ከዚህ በታች እናያቸዋለን፡፡
1.ልጆች ጥፋት ሲያጠፉ ቅጣትን እንደማረቂያ የምንጠቀም ከሆነ ወዲያውኑ ብንጠቀመው ተፈላጊውን ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ልጆች ያጠፉትን ጥፋት ከረሱ በኋላ የሚፈጸም ቅጣት ውጤታማ አያረግም፡፡
2.ልጆች ለምን እንደተቀጡ ያጠፉት ጥፋት እና የሚያስከትለው ችግር ቢነገራቸው ውጤታማ የመሆን እድል አለው፡፡
3.በሆነውም ባልሆነውም ነገር ቅጣትን መጠቀም ውጤታማ አያደርግም ፡፡ከዚህ ይልቅ ልጆችን በጣም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ብቻ መቅጣት ተፈላጊውን ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡
ሁለተኛ ምንጭ:http://www.mahderetena.com
አቶ በሱፍቃድ ዜና የሰዎችን እድገት በሚያጠና የስነበሃሪ ትምህርት ዘርፍ (Developmental psychology) ሁለተኛ ዲግሪ(ማስተርስ) ያለው ሲሆን ባሁኑ በልጆች አስተዳደግ እና በትምህርት ዙሪያ ወላጆችን የሚያማክር ድርጅት ከፍቶ በግሉ እየሰራ ያለ ወጣት ባለሙያ ነው ፡፡ለበለጠ መረጃ zbesufekad@gmail.com