የፊንጢጣ መዉጣት(Rectal prolapse) ምንድን ነዉ?

ዉድ የዶክተር አለ ተከታታዮች የፊንጢጣ መዉጣት የምንለዉ የወፍራም አንጀት የመጨረሻ ክፍል ከመደበኛ ቦታዉ ለቆ ወይንም ተንሸራቶ ሲከሰት ነዉ፡፡አብዛኛዉን ጊዜ ሰዎች የፊንጢጣ መዉጣትን ከፊንጢጣ ኪንታሮት ጋር ተመሳሳይ ሲያደርጓቸዉ ይታያሉ፡፡ነገር ግን የፊንጢጣ መዉጣት ቦታዉን ለቆ ሲወጣ ሲሆን የፊንጢጣ ኪንታሮት ደግሞ የደም ስር ሲያብጥ የሚከሰት ነዉ፡፡

የፊንጢጣ መዉጣት ሊያስከትሉ የሚችሉ መንስኤዎች

  • ረጅም ጊዜ የቆየ ድርቀት እና ተቅማጥ
  • ረዘም ላለ ጊዜ ማማጥ
  • የእድሜ መጨመር
  • የጡንቻ እና ጅማት መድከም
  • ፊንጢጣ እና ዳሌ አካባቢ የተከሰተ አደጋ
  • የነርቭ ጉዳት
  • የአከርካሪ አጥንት ጉዳት
  • የስኳር ህመም
  • የተወሳሰበ የሳንባ ችግር
  • የአንጀት ጥገኛ ትላትል
  • የፕሮስቴት እጢ ማደግ

የፊንጢጣ መዉጣት ምልክቶች

  • የታችኛዉ የሆድ ክፍል እና ፊንጢጣ ላይ ህመም/ምቾት አለመሰማት
  • ደም እና ዘለግላጋ የሆነ ፈሳሽ ከፊንጢጣ መዉጣት
  • ከፍተኛ ድርቀት
  • ሰገራ ከተቀመጡ በኋላ ያለመጨረስ ስሜት መሰማት
  • በፊንጢጣ በኩል የሚወጣ ስጋ ነገር መኖር
  • የፊንጢጣ መቆጣት/እብጠት
  • በሰገራ ወቅት ህመም

የፊንጢጣ መዉጣት እንዳይከሰት መከላከያ መንገዶች

  • በፋይቨር የበለጸጉ ምግቦችን አብዝተ መዉሰድ
  • ዉሃ አብዝቶ መጠጣት
  • ቋሚ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
  • የሰዉነት ክብደት ማስተካከል
  • ድርቀት እንዳይከሰት መከላከል

ለፊንጢጣ መዉጣት የሚደረግ ህክምና

የፊንጢጣ መዉጣት በቀዶ ህክምና ብቻ እንዲታከም ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር እና ሰገራ እንዲለሰልስ የሚሰጡ መድሐኒቶች አሉ፡፡

የታችኛዉ የሆድ ክፍል እና ፊንጢጣ ላይ የህመም ስሜት/ምቾት አለመሰማት፤ ሰገራ በሚቀመጡበት ወቅት ህመም እና ያለመጨረስ ስሜት፤ ደም የቀላቀለ ሰገራ እና በፊንጢጣ በኩል የሚወጣ ስጋ ነገር ካስተዋሉ በፍጥነት ሐኪሞዎን ያማክሩ፡፡

ምንጭ: ዶክተር አለ

Advertisement