የትኩረት ያለህ ለእንስሳት ጤና አጠባበቅ

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት እንዳላት ይነገራል፡፡ ሆኖም ከሀብቷ ይህንንም ያህል ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ምርትና ምርታማነቱም ዝቅተኛ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ነገሮች ደኅንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ መኖ ማቅረብ ይገኝበታል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መኖ ቸርቻሪዎች በሕግ አለመታቀፋቸው በደኅንነቱና ጥራት አጠባበቁ ላይ እክል ሆኗል፡፡ በዘርፉ የሚታየው ክፍተት ደግሞ በእንስሳት፣ በእንስሳት ተዋጽኦ (ወተትና ሥጋ) እና ተዋጽኦውን በሚጠቀሙ ሰዎች ጤንነት ላይ ችግሮችን ያስከትላል፡፡ የመኖ ዋጋ መናር ደግሞ ችግሮቹ እንዲባባሱና እንዲወሳሰቡ አድርጓል፡፡

ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተጠበቀ የእንስሳት መድኃኒት ለተጠቃሚው እንዲደርስ ጥረት ቢደረግም፣ በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶች የሚያስከትሏቸው ችግሮች እየተባባሱ መጥተዋል፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ የእንሰሳት መድኃኒቶች ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ሳይረጋገጥ ጥቅም ላይ መዋላቸው እንስሳትንና የእንስሳት ተዋጽኦን ለውጭ ገበያ በማቅረብ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ የመድኃኒቶቹ በሽታን መላመድም ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡   

ጠርዙ ዳና (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ፣ የመኖ ደኅንነትና ጥራት አጠባበቅ ላይ የሚታየው ክፍተት በእንስሳት ተዋጽኦ ላይ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ወተት ውስጥ ሻጋታ (አፍላቶክሲን) እንዲፈጠር ማድረጉ ነው፡፡ ሻጋታ ያለበትን ወተት የሚጠጣ ሕፃን ደግሞ ዕድገቱ ይቀነጭራል፣ ለጉበት ካንሰርም ይጋለጣል፡፡

መኖ የሚዘጋጀው የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችን በአንድ ላይ በማቀነባበር ሲሆን፣ በዘርፉ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ከ30 በላይ መኖ አቀነባባሪዎች እንዳሉ ዶ/ር ጠርዙ ይናገራሉ፡፡ ለመኖ ማቀነባበሪያ የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች፣ የቢራ፣ የሸንኮራና የዘይት ተረፈ ምርቶች፣ የበቆሎና የስንዴ ዱቄት፣ ሳር፣ ፉርሽካና ከውጭ የሚገባ ፕሪሚክስ (አሚኖ አሲድና ቫይታሚን) ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የተዘጋጀው መኖ ጥራቱና ደኅንነቱ ካልተጠበቀ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ጎላ ብሎ የሚታየው በችርቻሮ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ችግሩ የታየው ሕጋዊ ዕውቅና በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ የሠለጠነ የባለሙያም እጥረት ስለታከለበት ጭምር መሆኑን ያክላሉ፡፡

ከዚህም ሌላ በእርሻ ማሳ ላይ የበቀሉትና ለአጨዳ የደረሱት የበቆሎና የስንዴ ሰብሎች ዝናብ ከመታቸውና ከታጨዱም በኋላ እርጥበት ላይ ከተቀመጡ ለሻጋታ መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወደ ጎተራ ሲጓዙም ሆነ ሲከማቹ ሻጋታ በማይፈጠር መልክ ሊሆንና ከፍተኛ ጥንቃቄም ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡

‹‹የመኖ ደኅንነትና ጥራት አጠባበቅ አሳሳቢ ከመሆኑ ባሻገር በዋጋው መናር ሳቢያ ደግሞ የአቅርቦት እጥረት መፈጠሩም እንደ አንድ ዓብይ ችግር ይታያል፡፡ እጥረትም ሊፈጠር የቻለው ጥሬ ዕቃ የሆነውን ሳር፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ፋጉሎና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ባለሀብቶች ባለመኖራቸው ነው፡፡ ባለሀብቶች በዘርፉ የሚያገቡት የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ስለሌለው ነው፡፡

በዚህም የተነሳ አንዳንድ የዶሮና ዕርባታዎችና የወተት አምራቾች የተዘጉ ሲሆን፣ የወተት ዋጋም ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ በጥቃቅንና አነስተኛ እንደተደራጁ፣ ለዚህ አገልግሎት የሚውል የመኖ እጥረት በመኖሩ ግን እንቅስቃሴው ፍሬ አልባ እየሆነ እንደመጣም ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የእንስሳት መድኃኒት አምራቾች ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ የቀረው 97 በመቶ ያህል የእንስሳት መድኃኒት ከተለያዩ የውጭ አገሮች ነው የሚገባው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት በማይታይባቸው የቅርብና የጎረቤት አገሮች መከበቧ ለኮንትሮባንድ ንግድ ምቹ መደላድልን ፈጥሯል፡፡

በአንድ በኩል የኮንትሮባንድን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር፣ በሌላው በኩል ደግሞ ወደ አገር የሚገቡ መድኃኒቶች ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸውን የማረጋገጡ ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለና የማረጋገጡም ሥራ እየተከናወነ ያለው በተለያዩ ሦስት መንገዶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመድኃኒት አቅርቦትና ማከፋፈል እንቅስቃሴ ላይ ከባለሥልጣኑ ሕጋዊ ዕውቅናና የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፍኬት የተሰጣቸው ከ90 በላይ አስመጪዎችና ከአንድ መቶ የሚበልጡ ጅምላ አከፋፋዮች እንዳሉ ዶ/ር ጠርዙ ገልጸው፣ የጅምላ አከፋፋዮች መጋዘን፣ የመድኃኒቱን ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነት በማያጓድል መልኩ መዘጋጅቱንና የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ማቀፉንም በየወቅቱ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ሞጆ፣ ቦሌና ቃሊቲ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ያቤሎ፣ መቐለና ባህርዳር ስድስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች የኮንትሮባንድ መቆጣጠሪያ ኬላዎችንና ቁጥጥሩን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ እየሠራ ይገኛል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ከ2,000 በላይ የሚሆኑና ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው፣ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ሳይሆን የየክልሉ መንግሥታት አካላት የሚቆጣጠሯቸው ከ2,000 በላይ የእንስሳት መድኃኒት ቸርቻሪዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

 የችርቻሮ ንግድን የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ያላቸው የየክልሉ መንግሥታት የሚመለከታቸው አካላት እንደሆኑ፣ ባለሥልጣኑ የራሱን የሥራ ድርሻ ከመሸፈን አልፎ ለቁጥጥሩ ሥራ ተገቢውን ዕገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ዕገዛና ድጋፉ የሚያተኩረው በተሞክሮ፣ የልምድ ልውውጥ፣ በቅስቀሳና በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ ቀረፆ ወደ ሥራ እንደገባ፣ የስትራቴጂውም የትኩረት አቅጣጫ የሕገወጥ ንግድ አስከፊነት፣ ጥራቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ መኖ እንዲሁም ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ለእንስሳቱ ያላቸውን ፋይዳ በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሞያሌ፣ በዲላ፣ በኮንሶ፣ በአርባ ምንጭ፣ በኮምቦልቻ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በመተማ፣ በሁመራና በሌሎችም ሕገወጥ የእንስሳት ንግድ በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች የኅብረተሰብ ንቅናቄ መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር

Advertisement