በጣሊያን ታዋቂዋን አጂቱ ጉደታን መግደሉን ጋናዊው ሠራተኛዋ ለፖሊስ አመነ BBC

በጣሊያን ውስጥ ከፍየል ወተት በምታዘጋጀው አይብና ለስደተኞች መብት ተቆርቋሪነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ አጊቱ ጉደታ ቤቷ ውስጥ ተገድላ መገኘቷን ፖሊስ ማሳወቁን በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቢቢሲ አረጋገጠ።

የኤምባሲው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ደሳላኝ መኮንን እንደተናገሩት ትናንት ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ማጣራትና ምርመራ በአጊቱ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ተጠርጣሪ ስደተኛ ወንጀሉን መፈጸሙን እንዳመነ ገልጸዋል።

በሮም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የአጊቱ ጉደታን ሞት በተመለከተ በፌስቡክ ገጹ ላይ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፤ ግድያውን በተመለከተም ኤምባሲው ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቶሎ ተጣርቶ ይፋ እንዲደረግና ወንጀለኛው ለፍርድ እንዲቀርብ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አመልክቷል።

የአጊቱ ግድያ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በጣሊያኖችም ላይ ትልቅ ድንጋጤና ሐዘን የፈጠረ መሆኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ በተለይ በስደት ወደ ጣሊያን የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያንን በመርዳት ስለምትታወቅ ወንጀሉ በስደተኞች ዘንድ ታላቅ ሐዘንን አስከትሏል ብለዋል።

ፖሊስ እንዳለው አጊቱ ጉደታ ትሬንቲኖ ውስጥ በሚገኘው ፍራሲሎንጎ በተባለው ስፍራ ባለው መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት ደርሶባት አስከሬኗ አግኝቷል።

ምርመራ እያደረገ እንደሆነ የገለጸው ፖሊስ የአጊቱ ጉደታ ሞት ጭንቅላቷ ላይ በመዶሻ በመምታት የተፈጸመ የግድያ ወንጀል ሳይሆን እንዳልቀረ ገልጿል።

ከአስር ዓመት በፊት በስደት ወደ ጣሊያን የገባችው አጊቱ ጉደታ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አርብ ዕለት 43 ዓመት ይሆናት ነበር።

የዘረኝነት ጥቃት ይደርስባት ነበር

ጣሊያን ከጀርመን ጋር በምትዋሰንበት በተራራማዋ ትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ ለዓመታት የኖረችው አጊቱ፣ ዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶች ያጋጥሟት እንደነበር ለፖሊስ አመልክታለች።

አንዳንዶች በቆዳዋ ቀለም የተነሳ “አስቀያሚ ጥቁር እያሉ ይሰድቡኛል፤ ያለሁበትም ቦታ አገሬ እንዳልሆነ ይነግሩኛል” በማለት በግልጽ ያገጠሟትን የዘረኝነት ጥቃቶች ስትገልጽ ነበር።

ነገር ግን ‘ላ ሪፐብሊካ’ የተባለው የጣሊያን ጋዜጣ እንደዘገበው ፖሊስ በግድያው ዙሪያ የሚያደርገው ምርመራ በአንድ ወጣት አፍሪካዊ ላይ ያተኩራል ብሏል።

ወጣቱ ከዚህ በፊት በአጊቱ ላይ ጥቃትና ማስፈራሪያ ከሰነዘሩት ሰዎች መካከል እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ ምናልባት በገንዘብ ጉዳይ አለመግባባት ሊኖራቸው እንደሚችል ተገምቷል።.

አጊቱ የሚገጥማትን የዘረኝነት ጥቃት ይፋ ባወጣችበት ጊዜ የግዛቲቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኡጎ ሮሲ ድርጊቱን ተቃውመው ከጎኗ ቆመው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ “አጊቱ ስደተኛ ሆና የእንስሳት እርባታ ሥራዋን በግዛታችን ውስጥ ማከናወን መጀመሯ የትሬንቲኖን እንግዳ ተቀባይነትና ደጋፊነትን ያሳያል” ብለው ነበር።

አጊቱ በምትኖርበት ግዛት ውስጥ ሊጠፉ ተቃርበው ነበር የተባሉ የፍየል ዝርያዎችን በማርባት ከወተታቸው የተለያዩ ተዋጽኦዎችን እያመረተች ምርቷ ተወዳጅነትን እሷም ታዋቂነትን አትርፋ ነበር።

አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው አጊቱ ጉደታ ለስደት የተዳረገችው፣ በትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን የመሬት ነጠቃ በመቃወም በምትሰጠው አስተያየት፣ የግድያ ዛቻ ይደርሳት ስለነበረ ነው።

አጊቱ ጉደታ ከአስር ዓመት በፊት በመንግሥት የሚደርስባትን ጫና ሸሽታ ወደ ጣሊያን ከገባች በኋላ የስደተኝነት ፈቃድ አግኝታ የእንስሳት እርባታና የወተት ተዋጽኦ ምርት ሥራን በመጀመር በአጭር ጊዜ ስኬታማ በመሆን ለበርካታ ስደተኞች ምሳሌ ለመሆን ችላ ነበር።

በሥራዋ ዝናን ያተረፈችውን የአጊቱን ሞት በተመለከተ በርካታ የጣሊያን ጋዜጦች ጽፈዋል። ሁሉም አጊቱ በትሬንተን ግዛት ውስጥ ወደ ደረሰችበት ስኬት ለመብቃት ከባድ ፈተናዎችን ማሳለፏን የጠቀሱ ሲሆን፤ ባላት ጥንካሬና ቆራጥነት የዘረኝነት አመለካከቶችን ተጋፍጣ በምትኖርበት አካባቢ ተወዳጅነትን እንዳተረፈች ሁሉም መስክረዋል።

በአጊቱ ላይ በተፈጸመው ግድያ ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ምርመራ የተደረገበት ጋናዊ ስደተኛ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ወንጀሉን እንደፈጸመ ማመኑን ኮሪየር ዴላ ሴራ የተባለው የጣሊያን ጋዜጣ ምርመራውን ያካሄዱ መኮንኖችን ጠቅሶ ዛሬ ዘግቧል።

አጊቱ በምትሰራው የፍየል እርባታና የወተት ተዋጽኦ ምርት ሥራ ውስጥ ለበርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች የሥራ ዕድል እንደፈጠረች የተገለጸ ሲሆን፤ ግድያውን መፈጸሙን ያመነው ስደተኛም ለሦስት ዓመታት ተቀጥሮ መስራቱ ተነግሯል።

ተጠርጣሪው ከግድያው በኋላ በነበረው ምሽት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለሰዓታት በሰጠው ቃል ግድያውን መፈጸሙን አምኗል። የግድያው ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም በመጀመሪያ ላይ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

አጊቱ እዚያው ጣሊያን ውስጥ ሶሲዮሎጂ ተምራ ዲግሪ ያገኘች ሲሆን በተገደለችበት ዕለት የግብርና ሥራዋን ለማስፋፋት ከቅየሳ ባለሙያዎች ጋር ቀጠሮ ነበራት።

በወቅቱ በቀጠሮዋ መሰረት ባለመገኘቷ በሰዓት አክባሪነቷ የሚያውቋትን ሰዎችን አሳስቧቸው እንደነበር ተዘግቧል።

ከጎረቤቶቿ አንደኛዋም “ምን ሆና ነው የጠፋችው” በሚል ወደ ቤቷ በመሄድ ወደ መኝታ ቤቷ ሲገቡ ወድቃ እንዳገኟት ጋዜጣው ዘግቧል።

ከዚህ በኋላ ነበር ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ምርመራውን የጀመረው።

ምንጭ: BBC

Advertisement