‹‹ በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች በምጥ ከሚወልዱ እናቶች የመሞት ዕድላቸው ሶስት እጥፍ የሰፋ ነው ›

ህፃናት ይህችን ዓለም በሁለት መንገድ ይቀላቀላሉ በምጥ ወይም ደግሞ በኦፕሬሽን (surgical delivery by Cesarean section) ፡፡ በአሁኑ ወቅት የህክምና አማራጭ ያላቸው እናቶች አምጦ ከመውለድ ይልቅ በኦፕሬሽን መውለድን እንደተሸለ አማራጭ ሲወስዱ ይታያል ፡፡ ለመሆኑ በኦፕሬሽን መውለድ የተሻለ የሚያደርገው መቼ ነው?

በኦፕሬሽን መውለድ መቼ መወሰን አለበት?

– የጽንሱ አቀማመጥ በትክክል ካልሆነ ማለትም በእርግዝና የመጨረሻዎች ቀናት ጭንቅላቱ ወደታች ካልመጣ

– አምጦ መውለዱ ለእናትየው ወይም ደግሞ ለህፃኑ ህይወት አደጋ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ሲታመንበት

– ጽንሱ በጣም የፋፋ/የወፈረ/ ከሆነ እና የእናትየው ማህጸን ጠባብ ከሆነ

– በምጥ ወቅት ጽንሱ በቂ ኦክስጅን ካላገኘና የመተንፈስ ችግር ካጋጠመው

– መንታና ከዚያ በላይ ጽንስ ሲኖር

– የተራዘመ ምጥ ሲኖር

– እናትየው ከፍተኛ የደም ግፊት ካለባት፤ የስኳር በሽተኛ ከሆነች፣ የኤችአይቪ ቫይረስ ካለባት እንዲሁም ሌሎች አስጊ የሆኑ በሽታዎች ካሉ

– እናትየው ከዚህ ቀደም በቀዶ ጥገና የወለደች ከሆነች (ነገር ግን ብዙ ሴቶች ከዚህ በፊት በቀዶ ጥገና ቢወልዱም ቀጣዩንበተሳካ ሁኔታ በምጥ መውለድ ይችላሉ)

– ህጻኑ አካላዊ እክል ከገጠመው

ጥቅሙ?

– በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ እናቶችን እና የጽንስን ህይወት ይታደጋል

– እናቶች በምጥ ወቅት ሊሰማቸው የሚችለውን የተራዘመ ስቃይ ያስቀራል

ጉዳቱ?

– ጽንሱን ለማውጣት የሚቀደደው የሰውነት ከፍል ለመዳን ጊዜ ይወስዳል

– በሰውነት ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳም በቀላሉ የሚድን አይደለም

– የእናቶችን የሆስፒታል ቆይታ ያራዝማል

– በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች በፍጥነት አገግመው ልጆቻቸውን ለማጥባትም ሆነ ለመንከባከብ ይቸገራሉ

– የመጀመሪያ ልጃቸውን በኦፕሬሽን የወለዱ እናቶች ቀጣይ ልጆችን በተመሳሳይ ሂደት እንዲወልዱ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ይህም በማህጸን ግድግዳ ላይ ተደጋጋሚ ጠባሳዎች ያስከትላል፤ ቁስሉ በቶሎ ካልዳነ ደግሞ የማህጸን ግድግዳ ከሌላ የሰውነት ከፍል ጋር ሊጣበቅ ይችላል

– በምጥ ከሚወልዱ እናቶች ይልቅ በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች ለከፍተኛ ደም መፍሰስ ይጋለጣሉ

– ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድላቸውም ከፍተኛ ነው

– የደም መርጋት ሊከሰትባቸውም ይችላል

– በሚወለደው ልጅ ላይ ጉዳት ሊከሰት ይችላል

– በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች በምጥ ከሚወልዱ እናቶች የመሞት ዕድላቸው ሶስት አጥፍ የሰፋ ነው

– በኦፕሬሽን ሂደት ውስጥ የሽንትና የሰገራ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ሊጎዱ ይችላሉ ስለዚህ በኦፕሬሽን ለመውለድ ከመወሰንዎ በፊት ከሀኪሞ ጋር ስለ ጥቅሙና ጉዳቱን መወያየት አስፈላጊ ነው፡፡

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.