የገቢ መጠን መቀያየር ከልብ በሽታ ተጋላጭነት ጋር ይያያዛል

የገቢ መጠን ተለዋዋጭ መሆን የልብ በሽታ ተጋልጭነት መጠንን እንደሚጨምር አንድ ጥናት አመላከተ፡፡

ያልተጠበቀ የገቢ መለዋወጥ በተለይም በወጣቶች ላይ የመሞት እድልን በሁለት እጥፍ እንደሚያሳድግም ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናቱ ገቢያቸው ባልተጠበቀ መልኩ የሚለዋወጥ ሰወች ቋሚ ገቢ ካላቸው አንፃር  ለልብ በሽታ፣ በጭንቅላት ውስጥ ለሚከሰት ደም መፍሰስ እና ለልብ ድካም የመጋለጥ እድላቸው 50 በመቶ ከፍ ይላል ብሏል፡፡

የገቢ መለዋወጥ በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍ እያለ መምጣቱን የጥናቱ መሪ የሆኑትና በሚያሚ ሚሌር ዩኒቨርስቲ የህክምና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ታሊ ኤልፋሲ ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ ከፈረንጆቹ 1990 ጀምሮ ገቢያቸው ከ25 በመቶ በላይ የቀነሰባቸውን ሰዎች በማካተት የተካሄደ ነው።

በዚህም ከ2005 እስከ 2015 ባሉት ጊዜያት ከልብና የደም ቧንቧ ጋር ተያይዞ የተከሰተ የሞት መጠንና በሽታዎች ላይ ጥናቱ ትኩረቱን አድርጓል፡፡

በዚህም ቋሚ ያልሆነ ገቢ ወይም የገቢ መለዋወጥ በዋነኝነት በጥቁር እና ሴቶች ላይ በብዛት እንደሚስተዋልም የጥናት ቡድኑ ገልጿል።

በአሜሪካ ከአራቱ አንዱ ሞት የሚከሰተው በልብ በሽታ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ የስብ ክምችት እና ሲጃራ ማጨስ ለበሽታው አስተዋፅኦ እንዳላቸው  ተነግሯል፡፡

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.