የነርቭ ህመም

ሰውነት ውስጥ ቁጥራቸው በአስርሺዎች የሚሆን ነርቮች አሉ። ነርቮች በአእምሮ እና ቀሪው ሰውነት መሃከል መልእክት ያስተላልፋሉ። ጡንቻዎቻችን እንዲቀሳቀሱ ከአእምሮ ወደ ጡንቻ መልእክት የሚልኩ ነርቮች አሉ። ሌሎች ነርቮች ደግሞ የህመም፣ ጫና እና ሙቀት መልእክት ከሰውነት ወደ አእምሮ ያስተላልፋሉ።

መልእክቶችን በትክክል ለማስተላለፍ እያንዳንዱ ነርቭ በውስጡ ትናንሽ ፋይበሮች ይይዛል። በውጭ በኩል ደግሞ ፋይበሮቹን በሚከላከል ሽፋን ተሸፍኗል።

አንዳንድ ግዜ ነርቮች ጉዳት የሚያስተናግዱ ሲሆን የህመሙ ሜዲካል ስም ኒውሮፓቲ ይባላል። ነርቭ የሚጎዳበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ነርቭ በሚደርስበት ከፍተኛ ጫና ወይም መቆረጥ እና መለጠጥ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ሌላ የነርቭ ጉዳት መንስኤዎች የስኳር በሽታ፣ የተደጋገመ እንቅስቃሴ፣ የላይም በሽታ፣ ከመጠን በላይ ማጨስ፣ ለመርዛማ ንጥረነገሮች መጋለጥ፣ ኢንፌክሽን፣ እና እንደ ሄፕታይተስ ሲ፣ ዲፌትሪያ፣ ኤችአይቪ አይነት በሽታዎች ናቸው።

መንስኤው ምንም ሆነ ምን የነርቭ ጉዳት ምልክቶች ቀስ በቀስ እየዳበሩ ነው የሚታዩት። ምልክቱ የሚታይበት ቀን ቀረበም ራቀም ጉዳት እንዳጋጠመን የሚነግሩን ምልክቶች መታየታቸው አይቀርም። ሰውነትዎ የሚከተሉትን ምልክቶች ካሳየ ዶክተር በግዜ ማማከር ተገቢ ነው።

የነርቭ ጉዳት ምልክቶች እነሆ፦

1) መደንዘዝ

ስሜታዊ ነርቮች(sensory nerves) መጎዳታቸውን የምናውቅበት የመጀመርያው ምልክት የመደንዘዝ እና የመውረር ስሜት በእጅ፣ በጣት፣ በእግር፣ እና በእግር ጣቶች ላይ ሲፈጠር ነው። ስሜታዊ ነርቮች ስራቸው የስሜት መልእክት መላክ ሲሆን ጉዳት ሲያጋጥማቸው ቆይቶ ወደ መደንዘዝ የሚቀየር የመውረር ስሜት ይሰማናል። በግዜው ተገቢ ህክምና ካላገኘ ይህ ስሜት ወደ ሌሎች የሰውነት አካሎች ሊዛመት ይችላል። ህመሙ ከግዜ ጋር እየጨመረ የቀንተቀን ኑሮአችንን ያስተጓጉላል። እጅ እና እግር ላይ ለሚፈጠር የመደንዘዝ ስሜት ሌሎች መንስኤዎች እግር እና እጅ ላይ የተፈጠረ ከፍተኛ ጫና፣ ለብርድ መጋለጥ፣ እንቅስቃሴ የሌለበት የአኗኗር ዘይቤ እና የቫይታሚን ቢ12 እና ማግኒዚየም እጥረት ናቸው።

2) ህመም

ሌላ የነርቭ ህመም ምልክት የሚሰነጥቅ ወይም የሚያቃጥል የህመም ስሜት ነው። የዚህ አይነት ስሜት እጅ እና እግር ላይ የሚፈጠር ሲሆን ከሌላ የህመም ስሜት ይለያል። ህመሙ የሚፈጠረው ስሜታዊ ነርቮች ላይ በተፈጠረ ጉዳት ነው። ስሜት በአግባቡ ከአእምሮ ወደ ቆዳ መተላለፍ ካልቻለ የተጎዳው ቦታ ላይ ከፍተኛ ህመም ሊሰማን ይችላል።

የህመሙ ቦታ በተጎዳው ክልል ዙሪያ ብቻ ወይንም ሰፊ የሰውነት ክልል ላይ ሊፈጠር ይችላል። ህመሙ ብዙ ግዜ በምሽት ይባባሳል። ከነርቭ ጉዳት ውጪ የስኳር በሽታ፣ የቫይታሚን ቢ12 እጥረት ወይም የጀርባ አጥነት ሰረሰር ላይ የተፈጠረ ጉዳት ለከባድ የህመም ያጋልጠናል።

3) የጡንቻ ድካም

ጡንቻ እንዲቀሳቀስ የሚያደርገውን መልእክት የሚያስተላልፉ ነርቮች ላይ የደረሰ ጉዳት የጡንቻ ድካም ይፈጥራል። አልፎም ጡንቻን የመቆጣጠር ችሎታ ሊያሳጣ ይችላል። ለጡንቻችን የሚላከው መልእክት በአግባቡ ካልተላለፈ መራመድ እንቸገራለን። በእጃችን እቃዎች ለማንሳት እና ጭብጥ አድርጎ መያዝ ይከብደናል። በነርቭ ጉዳት ምክንያት ጡንቻ ጥቅም ላይ የሚውልበት ግዜ ሲቀንስ እራሱ እየደከመ ይመጣል።

ጡንቻ መዳከም ከነርቭ ጉዳት ውጪ እንደ ፓርኪንሰን በሽታ፣ የዲስክ መንሸራተት፣ ስትሮክ የመሳሰሉ ህመሞች መንስኤው ይሆናሉ።

4) የጡንቻ መሸማቀቅ

የእንቅስቅሴ ነርቮች ላይ የደረሰ ጉዳት የጡንቻ መሸማቀቅ እና መሳሳብ ሊያመጣ ይችላል። የጡንቻ መሸማቀቅ እና መሳሳብ በራሱ የተጎዱት ነርቮች ላይ በሚፈጥረው እንቅስቃሴ ጉዳቱን ሊያባብስ ይችላል። የጡንቻ መሸማቀቅ የሚፈጠረው የእንቅስቃሴ ነርቮች በብዛት ሲሰሩ ነው። የመሸማቀቅ ስሜት ክብደቱ ቀላል፣ መሃከለኛም ወይንም በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል።

5) የላብ ችግር

የሰውነት አካልን የሚረዱ ነርቮች ሲጎዱ አውቶኖሚክ ኒውሮፓቲ የሚባል ህመም ሊያስከትል ይችላል። አውቶኖሚክ ነርቮች ሲጎዱ የላብ ችግር ሊፈጥር ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ላብ ሲፈጠር ሌሎች ላይ ደግሞ የላብ መቀነስ ይታያል። ላብ በአግባቡ ካልመነጨ ሰውነታችን ሙቀቱን በአግባቡ መቆጣጠር አይችልም። በከፍተኛ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት ችግሩ ይገዝፋል።

6) ሽንት ቤት መመላለስ

የሽንት ፊኛ ሽንትን በደንብ እንዲይዝ ብዙ ነርቮች አብረው መስራት አለባቸው። የነርቭ ጉዳት ሲፈጠር የሽንት ፊኛ ሽንትን ቶሎ ቶሎ ለማስወገድ ይሞክራል። የነርቭ ጉዳት የሽንት ፊኛ ጡንቻዎች የሚያደርጉትን መኮማተር እና መላላት በተገቢው መልኩ እንዳያደርጉ ያስተጓጉላል። የሽንት ፊኛ ችግር ሌላ መንስኤ ሊኖረው ይችላል። ልጅ በወለዱ እናቶች እና የስኳር በሽታ ታካሚዎች ላይ የሚፈጠር ችግር ነው።

7) ከባድ ራስምታት

ኤሌክትሪክ ንዝረት የሚመስል አጭር ግዜ የሚቆይ ከባድ ራስምታት የነርቭ ጉዳት ምልክት ሊሆን ይችላል። ህመሙ የኦክሲፒታል ኒውራልጂያ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል። ኦክሲፒታል ኒውራልጂያ አንገት ላይ ያለ የነርቭ መቆንጠጥ በሽታ ነው። ህመሙ የላይኛው አንገት ክፍል ወይም ጭንቅላት ጀርባ ላይ ይፈጠራል።

8.ሰውነት ሚዛን መጠበቅ መቸገር

የሰውነት ሚዛን መጠበቅ መቸገር ወይም መንገዳገድ ሌላ የነርቭ ጉዳት ምልክት ነው። ወድቀው ሊጎዱ ስለሚችሉ ይህን ምልክት ችላ ማለት የለብዎትም። የነርቭ ጉዳት አእምሮ የሰውነትን እንቅስቃሴ በአግባቡ እንዳይቆጣጠር ያደርጋል። ይህ ሁኔታ ወድቀው እንዲጎዱ ሊያደርግ ይችላል። የሰውነት ሚዛን መጠበቅ መቸገር የፓርኪንሰን ህመም ምልክት ሊሆን ይችላል።

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.