40 ሚሊየን የሚሆኑ የስኳር ህመምተኞች በ2030 ኢንሱሊን እንደማያገኙ ተገለፀ

የስኳር ህመምተኞች ቁጥር  በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ  ህመምተኞች ኢንሱሊን ለማግኘት እንደሚቸገሩ አንድ ጥናት አመላከተ።

በፈረንጆቹ 2030 በደረጃ 2 የስኳር ህመም የተጠቁ 79 ሚሊየን ሰዎች ህመማቸውን ለማስታገስ ኢንሱሊን የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፥ የአቅርቦት መጠኑ በዚህ ደረጃ የሚቀጥል ከሆነ ግማሽ የሚሆኑት ብቻ በቂ ኢንሱሊን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡

የመድሃኒቱ አቅርቦት ሊሻሻል ይገባል ያሉት ተመራማሪዎቹ በተለይ በአፍሪካ፣ እስያ እና ኦሽኒያ አካባቢዎች ተፅዕኖው ሊበረታ እንደሚችል አሳስበዋል።

ጥናቱ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢንሱሊን አቅርቦት በቂ እንዳልሆነ ማሳየቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህን የጤና ችግር በአፍሪካና እስያ ለመቅረፍ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና በአለም አቀፍ ደረጃ የስኳር መድሃኒቶችን አቅርቦት ለማሻሻል  ቢንቀሳቀስም፥ እጥረቱ እንዳለና ህመምተኞች መድሃኒቱን ለማግኘት እንደሚቸገሩ ተነግሯል፡፡

ጥናቱ በአለም አቀፍ ደራጃ በአሁኑ ወቅት ያለው 406 ሚሊየን የስኳር ህመምተኞች  ቁጥር በ2030 ወደ 511 ሚሊየን እንደሚያድግ ግምቱን አስቀምጧል።

በደረጃ 2 የስኳር ህመም የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በቀጣዮቹ 12 ዓመታት ከአመጋገብ ስርዓት፣ ከከተማ መስፋፋትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ተያይዞ እንደሚጨምርም ተጠቁሟል፡፡

የኢንሱሊን ህክምና ውድ መሆኑን ያመላከተው ጥናቱ የመድሃኒት ንግዱ በሶስት አምራቾች የበላይነት እንደሚመራም ጠቅሷል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.