ፓርላማው ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሾመ

መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ በስደት ይኖሩ ከነበረበት አሜሪካ የተመለሱት የቀድሞ ፖለቲከኛ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል፡፡

መንግስት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በአዲስ መልክ ለመተካት የወሰነው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ የተጀመረው የጥረት አካል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ ቦርድ ተዓማኒ ለማድረግ ተቋሙን የማዘመንና ማሻሻል ከማድረግ በተጨማሪ ብቁ የሆነ መሪ እንደሚያስፈልገው በማመን ወ/ሪት ብርቱካን ለዕጩነት ቀርበዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን በቀላሉ እጅ የማይሰጡና በሁሉም ዘንድ ተዓማኒነት ይኖራቸዋል ብለን እናምናለንም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የፓርላማ አባላቱ በዕጩ ሰብሳቢዋ ዙሪያ ከገልተኛነታቸውና ከዜግነታቸው አንፃር የተያያዙ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ምላሽ በዕጩ ሰብሳቢዋ ላይ ተገቢውን ማጣራት መደረጉን እንደተረጋገጠ ተናግረዋል፡፡በአሜሪካ በነበሩበት ወቅትና የሚመሩትን “ናሽናል ኢንዶውመን ፎር ዲሞክራሲ” የሚባል ተቋም ኃላፊነት ለቀው ነው እንዲመጡ ያደረግነው ብለዋል፡፡

እጩዋ ዋናው ነገር በህገ መንግስቱ መስራታቸውን ማረጋገጥ የሁላችንም ፍላጎት ከለሆነ ይህም አሳሳቢ ጉዳይ አይሆንም ብለዋል፡፡

ዜግነታቸውም ቢሆን ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን መረጋገጡም ተመልክቷል፡፡
ፓርላማው በዕጩ ሰብሳቢዋ ላይ ውይይት ካደረገ በኃላ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን ሰብሳቢ እንዲሆኑ በ4 ታቃውሞ በ3 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ከተመረጡ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነትን በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁትን ወ/ሮ ሳሚያ ዘካርያን በመተካት የሚመሩ ይሆናል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከዚህ በፊት በፖለቲካው አለም የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትና የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስራች በመሆናቸውም ይታወቃሉ፡፡

በወቅቱ በመንግስት ተቀዋሚነታቸው ለሁለት ጊዜ ያህል ለእስር ተዳርገው መፈታታቸውም ይታወሳል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ከእስር እንደወጡም ኑሯቸውን በስደት አድርገው በአሜሪካ ላለፉት ጥቂት ዓመታት መግፋታቸውና መንግስት ባደረገላቸው ጥሪ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ምንጭ: Ethiopian Broadcasting Corporation

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.