ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ዜጎች በመዳረሻ ቪዛ መሥጠት ጀመረች

በስላባት ማናየ

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ዜጎች በመዳረሻ ቪዛ መሥጠት መጀመሯን መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች በተገኙበት ይፋ አደረገች።

በዛሬው ዕለት ከትናንት በስቲያ በይፋ በተጀመረው የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎትን በተመለከተ ለአምባሳደሮች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ፥ ኢትዮዽያ ለአፍሪካ ሀገራት ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ መስጠት መጀመሯ ፓን አፍሪካኒስትነቷን ዳግም ያጠናከረችበት ታሪካዊ ሁነት ነው ብለዋል።

ሊቀመንበሩ ኢትዮዽያ የፓን አፍሪካኒስት እንቀስቃሴ መስራች እና ባለውለታ መሆኗን በመግለፅ አሁን ደግሞ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና የሆነቸው አዲስ አበባ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሷ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሀላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እያራመዱት ያለው ፓን አፍሪካዊ እንቅስቃሴ የሚያኮራ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ውሳኔ ማሳለፋቸው እንደሚያኮራና ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ሊቀመንበሩ ይህ የኢትዮጵያ ተግባር ለሌሎች አፍሪካዊያን በመልካም አብነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 ለማሳከት ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው፥ ኢትዮዽያ በአፍሪካ አጀንዳዎች አንደማትደራደርና ሃላፊነቷንም አጠናክር እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት በክፍል አህጉር እና አህጉር ደረጃ ለማሳካት የታሰበውን የምጣኔ ሀብት ውህደት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በዋናነት ወጣቶችና ሴቶች በአህጉራቸው ውስጥ በነጻነት በመንቀሳቀስ የራሳቸወን የስራ እድል እና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲፈልጉ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለቱሪዝም፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴን ከማሳደግ፣

እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ከፀጥታ ፣ ከህግ ወጥ የንግድ ልወውጥ እና ኮንትሮባንድ አኳያ ሊፈጠሩ የሚችለውን ክፍተቶችን ለመድፈን በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለበረራ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የኢትዮዽያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተናግረዋል።

የኢትዮዽያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከዚህ አኳያ የሚኖረውን ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ነግረውኛል።

በመድረኩ የተሳተፉት የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎቱ አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካና አስተዳደር መዲና መሆኗን ያረጋገጠችበት ውሳኔ በማለት ገልፀዋል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.