ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፡ በሚያውቋቸው ሰዎች አንደበት

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በተለያየ አጋጣሚ የሚያውቋቸው ብዙዎች ስለ እርሳቸው አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ ነው። በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ብዙዎች ስለርሳቸው ብዙ ብለዋል፤ ብዙ እያሉም ነው።

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን ለረዥም ጊዜ በሥራ አጋጣሚ በቅርበት የሚያውቋቸው ስለ እርሳቸው ምን ይላሉ?

“በራ ብቁና ፀባየ ሸጋ ናቸውዲና ሙፍቲ (በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር)

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አዲሲቷን ርእሰ ብሔር “ብቁና ጸባየ ሸጋ” ሲሉ ያሞካሿቸዋል። አምባሳደር ሳሕለወርቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተለያዩ ኃላፊነቶች አገራቸውን ማገልገላቸውን ከጠቀሱ በኋላ ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል ከሚባሉ የውጭ ጉዳይ ባልደረቦች አንደኛዋ እንደነበሩ ያወሳሉ።

“እንደ ውጭ ጉዳይ ባልደረባ ረዥም ጊዜ ነው የማውቃቸው። እኔ አምባሳደር በነበርኩበት ወቅት እሳቸው በዋና ኃላፊነት፤ እኔ ዋናው መሥሪያ ቤት በነበርኩበት ወቅት ደግሞ በአምባሳደርነት በሴኔጋል፣ በጅቡቲም በፈረንሳይም ሲያገለግሉ በደንብ አውቃለሁ።” የሚሉት አምባሳደር ዲና፣ ሳሕለወርቅን “ውክልናቸውን በሚገባ ሙያዊ ብቃት የተወጡ መልካምና ፀባየ ሸጋ።” ሲሉ ስለርሳቸው የሚያውቁትን ይመሰክራሉ።

አምባሳደር ዲና በሚመሩት በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲው ውስጥ በሚዘጋጁ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች “አምባሳደር ሳሕለወርቅ ዝግጅቶቹን ከሚያደምቁልን ሰዎች መሀል ዋንኛውነበሩ” ሲሉም ያስታውሷቸዋል።

“እዚህ በኬንያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ልዑክ ሆነው ውክልናቸውን በሚገባ ሙያዊ ብቃት የተወጡ በሥራቸውም የተዋጣለቸው ባለሙያም ነበሩ።”

“አዲስና ጀማሪ ባለሙያዎችን በጣም ያግዛሉ” አቶ ዘሩባቤል ጌታቸው

ከአምባሳደር ሳሕለወርቅ ጋር በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ውስጥ አብሯቸው የሠራው አቶ ዘሩባቤል ደግሞ ስለርሳቸው የሚከተለውን ይላል።

በኬንያ ናይሮቢ ተመድቤ ስመጣ መጀመሪያ ያገኘኋቸው እሳቸውን ነበር። በጣም ትሁት ናቸው፤ ቢሯቸውም ሁል ጊዜ ክፍት ነው። እኔን ከተቋሙ ኃላፊዎች ጋር በማስተዋወቅና እሳቸው የሄዱበትን መንገድ በማሳየት ረድተውኛል፣ አግዘውኛልም።

በተለይም ጀማሪና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሠራተኞችን በጣም ይደግፉ ነበር።

እዚህ ናይሮቢ ላይ የተለያዩ አገራት ልዑካን የኮሚቴ ስብሰባ ነበረን እና ፕሬዝዳንት ሆነው የመመረጣቸው ዜና ከተሰማ በኋላ ሁሉም ወደ እኛ መጥተው በስሜት ነበር ደስታቸውን የገለፁልን። ይህ ስለነበራቸው ቆይታ የሚናገር ነው።

የሥራ ደረጃቸው ኑሯቸውም እንደዚያው በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ስለ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ምን እንደሚመስል መናገር ባልችልም እኛን ዝቅ ብለው ስለ ኑሯችን ያኛው ይሄኛው እንዴት ሆነ ብለው ይጠይቁ ነበር። ስለዚህ በማኅበራዊ ሕይወታቸውም ሙሉና ቀና ሰው እንደሆኑ አምናለው።

በሥራ አጋጣሚ ከሚያውቋቸው ሰዎች በተጨማሪ ሌሎችንም የአምባሳደር ሳሕለወርቅ ርእሰ ብሔርነት ምን ስሜት ፈጠረባችሁ ስንል ጠይቀናቸው ነበር።

“የሴቶችን አቅም ያሳያል”ረድኤት ከፍአለ (የሎው ሙቭመንት አባል )

የአምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዘዳንት ሆኖ መሾም ትልቅ ትርጉም አለው።በመጀመሪያ ደረጃ የሴቶችን አቅም፤ሴቶች በዚህ ዓይነቱ ኃላፊነት መምራት እንደሚችሉ ያሳያል።

ከቀናት በፊት አስር ሴት ሚኒስትሮች መሾማቸውን ተከትሎ የአምባሳደር ሳህለወርቅ ሹመት ሲታይ በአጠቃላይ እንደማኅበረሰብ የሴቶችን መሪነት እንድንለምደው የሚያደርግ ነው። ይህ ልምድ ደግሞ ለወደፊቱ ሴቶችን ለዚህ ዓይነቱ ትልቅ ኃላፊነት መሾም እንዲቀለን ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።

በአጠቃላይ ሹመታቸው ከተምሳሌትነት አንፃር ያለው ጠቀሜታም ለኔ ጉልህ ነው።

“የተመረጠቸው እናት ናትወ/ሮ አበባ ገብረሥላሴ (የመቀሌ ነዋ)

በኢትዮጵያ ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆና መመረጧ በጣም ደስ ይለኛል። የተለየ ነገር እንኳ ባይመጣ አሁን ኢትዮጵያ ላይ በጣም ችግር የሆነው የሰላም መደፍረስና ሙስና በመሆኑ የተመረጠችው ደግሞ እናት በመሆኗ ነገሮች ይቀየራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ምክንያቱም እናት ለሰላም ብዙ ጥረት ታደርጋለች።እናት ለሰላም ትፀልያለች፤ ብዙ ትሞክራለች፤ ፍትህ ታመጣለች። ሁከት ሲፈጠር ልጄ፣ባሌን እና ወንድሜን ነው የሚጎዳው ብላ ሰላምን ፍለጋ ብዙ ትጥራለች። ከዚህ አንጻር “የተመረጠችው እናት ናት” እላለሁ።

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.