አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ የኢፌዴሪ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ | The First Female President of Ethiopia

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት ልዩ ስብሰባቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል ፡፡

ፕሬዝዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ፈፅመው ኃላፈነታቸውን በትጋትና በታማኝነት አገርና ህዝብን ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ላለፉት አመስት ዓመታት በኃላፊነት ላይ የነበሩትን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ከተመራጯ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የድፕሎማሲ ታሪክ ከአገር እስከ አለም አቀፍ ተቋማት ድረስ ኢትዮጵያን በመወከል ያገለገሉ አለም አቀፍ ዲፕሎማት ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜም በተባበሩት መንግስታት ደርጅት የዋና ፀሀፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ እና በተመድ የህብረቱ ተጠሪ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

የከፍተኛ ትምህርታቸውን በፈረንሳይ የተከታተሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ አገራት በተለይም በሴኔጋል ፣በማሊ ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ጊኒ፣ ኬፕ ቬርዴ እና በጅቡቲ በአምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያን በመወከል በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ልዩ መልዕክተኛ ሆነውም ሰርተዋል፡፡በፈረንሳይም የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ከእነዚህና ከኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊነት ቦታዎች ባሻገር በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ልዩ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነውም አገልግለዋል፡፡

አምባሳደሯ በቅርቡ የተመድ የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በአንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከመሾማቸውም በፊትም፣ በዋና ፀሀፊ ባንኪሙን ዘመን ኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉም ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከተመሰረተ ወዲህ ኢትዮጵያ ሶስት ፕሬዝዳንቶችን አፈራርቃለች፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያን ከ1987 ወዲህ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስና እና ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ናቸው፡፡

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች ከተመረጡበት ከዛሬ ጥቅምት 15፣2011 ጀምሮ 4ኛው የኢፊዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው የሚያገለግሉ ይሆናሉ፡፡

Advertisement

7 Comments

Comments are closed.