የዓለማችን ረዥሙ ቻይናን ከሆንግ ኮንግ የሚያገናኘው ባህር አቋራጭ ድልድይ ተከፈተ

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ግንባታው 9 ዓመታትን የፈጀውን የዓለማችንን ረዥሙን ባህር የሚያቋርጥ ድልድይ መርቀው ከፈቱ።

የድልድዩ አካል የሆኑ መንገዶችን ጨምሮ ርዝመቱ 55 ኪ.ሜ ሲሆን ሆንግ ኮንግን ከማካኡ እንዲሁም የቻይናዋን ዡሃይ ከተማን ያገናኛል።

የድልድዩ ግንባታ የተጠናቀቀው ከተያዘለት ጊዜ ዘግይቶ ሲሆን 20 ቢሊየን ዶላር ወጪንም ጠይቋል።

በግንባታው ወቅት ቢያንስ 18 ሰራተኞች ህይወታቸውን ቢያጡም ቻይናውያኑ ድልድዩን እውን ከማድረግ አልሰነፉም።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ከማካኡ እና ሆንግ ኮንግ መሪ ጋር በመሆን የምረቃው ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

ድልድዩ ነገ ለትራፊክ ክፍት ይደረጋል ተብሏል።

ድልድዩ የመሬት መንቀጥቀጥን እና አውሎ ንፍስን እንዲቋቋም ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፤ 400 ሺህ ቶን ብረት ለግንባታው ጥቅም ላይ ውሏል። የብረቱ መጠን የፈረንሳዩን ኤፍል ማማ አይነት 60 መገንባት ያስችላል ተብሎለታል።

ድልድዩ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እንዳይገታ በሚል 6.7 ኪ.ሜ የሚሆነው አካሉ በሰው ሰራሽ ዋሻ መልክ ከባህሩ ስር ተገንብቷል።

የፕሮጀክቱ አካል የሆኑ ቢሊየን ዶላሮች ፈሰስ የተደረገባቸው ሁለት ሰው ሰራሽ ደሴቶች በባህሩ ላይ ተገንብተዋል።Image copyrightGETTY IMAGES
አጭር የምስል መግለጫየፕሮጀክቱ አካል የሆኑ ቢሊየን ዶላሮች ፈሰስ የተደረገባቸው ሁለት ሰው ሰራሽ ደሴቶች በባህሩ ላይ ተገንብተዋል።

ከዡሃይ እስከ ሆንግ ኮንግ ይደረግ የነበረው ጉዞ 4 ሰዓት ይፈጅ ነበር። ድልድዩ ግን የጉዞውን ርዝመት ወደ 30 ደቂቃ አሳጥሮታል።

በድልድዩ ላይ ለመጓዝ ክፍያ የሚጠይቅ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት ቀደም ብለው ድልድዩ በቀን እስከ 9200 ተሽከርካሪዎችን ያስተናግዳል ብለው ገምተው ነበር።

የባህር እንስሳት ላይ ጉዳት ያስከትላል በሚል የድልድዩን ግንባታ የነቀፉ አልጠፉም።

ከምድር ገጽ ላይ እየጠፉ የሚገኙ እንደ ነጫጭ የቻይና ዶልፊን መሰል እንስሳቶች ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል ይላሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.