በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

ትምኒት ገብሩImage copyright: TIMNIT GEBRU አጭር የምስል መግለጫትምኒት ገብሩ

የተወለደችው እንደ አውሮፓውያኑ በ1983 ነው። ትምኒት ገብሩ ትባላለች። በ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ባለሙያዎች አንዷ ነች። አሁን ካሊፎርንያ ውስጥ የምትኖረው ትምኒት ጉግል ውስጥ ሪሰርች ሳይንቲስት ናት።

በ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ የጥቁር ሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ‘ብላክ ኢንኤአይ’ የተባለ ተቋምን ከመሰረቱት አንዷ ናት። የፈጠራ ሥራዎችን አካታችነት በሚፈትሹ ጥናቶቿ፤ እንዲሁም ቴክኖሎጂና የሰብአዊ መብት ጥያቄን በማስተሳሰርም ትታወቃለች። ትምኒት ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ያደረችው ቃለ ምልልስ እነሆ።

እስኪ ስለ አስተዳደግሽ አጫውችን. . .

ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ነው። መዋለ ህጻናት ቅድስት ሀና፤ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ናዝሬት ስኩል ተማርኩ። አስረኛ ክፍል ስደርስ ለአንድ ዓመት አየርላንድ ሄድኩ። ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርስቲ እዚህ አሜሪካ ጨረስኩ።

ትምኒት በትግርኛ ምኞት ማለት ነው። እናትና አባቴ ወንድ ልጅ፤ እህቶቼ ደግሞ ሴት እንድትወለድ ነበር የፈለጉት። ስወለድ እህቶቼ ትምኒት አሉኝ። የመጨረሻ ልጅ ነኝ። ህጻን ሳለሁ ትምህርት እወድ ነበር። ስታመም ራሱ ከትምህርት ቤት መቅረት አልወድም ነበር። ሒሳብና ፊዚክስ በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ዘፈንና እስክስታም በጣም ነበር የሚያስደስተኝ። እንዲያውም እህቴ ከ 30 ዓመት በፊት ስዘፍንና ተረት ሳወራ ቀድታኛለች።

አዘውትረሽ የምትሰሚው፣ የምትዘፍኝው ዘፈን ነበር?

በጣም የምወደው ዝንቦችን ስለማጥፋት የተዘፈነውን ነው። [ሳቅ እየተናነቃትና እያንጎራጎረች] “ልጆች ልጆች እንተባበር. . . ዝንቦቹን ለማጥፋት ከሰፈር” የሚለውን. . .

ወደ ሳይንሱ ያዘነበልሽው በዚህ አይነት ሙዚቃ ተስበሽ ይሆን?

ከዚህ ጋር የሚያያዝ አይመስለኝም። ወደ ሳይንስ ያዘነበልኩት አባቴ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ስለነበረ ነው። በአስር ዓመት የሚበልጡኝ ሁለት እህቶቼም ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ነበር ያጠኑት።

እንደ ጥቁር ሴት የአሜሪካን ኑሮ እንዴት አገኘሽው?

መጀመሪያ ደስ አላለኝም ነበር። እዚህ ሀገር የተለያየ የክፍል ደረጃ (ኦነር፣ ስታንዳርድ የሚባል) አለ። መጀመሪያ ትምህርት ቤት የሄድኩ ቀን ልዩነቱን ስላላወቅኩ ለኬምስትሪ ‘ስታንዳርድ’ የሚባል ክፍል ሄድኩ። አስተማሪው በዛ ዓመት የሚያስተምረውን ሲናገር «ይህንን ባለፈው ዓመት አየርላንድ ተምሬዋለሁ የሚቀጥለው ክፍል ልግባ» አልኩት።

«ብዙዎች እንዳንቺ ከሌላ ሀገር መጥተው በጣም ከባድ ትምህርትን የሚወጡ ይመስላቸዋል። የዚህን ሀገር ፈተና ብትፈተኝ [ግን] ትወድቂያለሽ» አለኝ። የማያውቀኝ ሰው ለምን እንዲህ ይለኛል? ብዬ ተገረምኩ። ብዙ አስተማሪዎች ጥሩ ውጤት ሳመጣ ይገርማቸው ነበር።

ኮሌጅ ለማመልከት የሚያግዝ አማካሪ «የትም አትገቢም» ብሎኛል። እናቴ «ለምን ልጄን እንዲህ ትላታለህ? ፈተና ፈትናት እንጂ ማስፈራራት አትችልም» ብላው ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ዲፕረስድ ሆኜ [ተደብቼ] ነበር ያሳለፍኩት። ኮሌጅ የተሻለ ነበር። ሥራው ላይ ስንመጣ፤ በኛ ሙያ ብዙ ሴቶች የሉም። ብዙ ጥቁሮች የሉም። ስለዚህ በማሰብ ብዙ ስትናደጂ ከስራሽ ትርቂያለሽ። [አንዳንዴ] ስለ ሌላ ነገርም ማሰብ አለብሽ።

ወደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የገባሽው እንዴት ነው?

ወደ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ መግባት እፈልጋለሁ ብዬ አይደለም የገባሁት። ፒኤችዲ ጀምሬ መሀል ላይ ነው የገባሁበት። ያኔ ብዙ ሰው ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ አይለውም ነበር። በ’ሜዲካል ኢሜጂንግ’ ዘርፍ ላይ ፍላጎት ነበረኝ። ለምሳሌ ገጠር የሚኖሩና ሆስፒታል የማያገኙ ሰዎች በስልካቸው እንዴት ህክምና ማግኘት እንደሚችሉ እያጠናሁ ነበር። ‘ኦፕቲክስ’ የሚባል የፊዚክስ ስፔሻሊቲ [ዘርፍ] እያጠናሁ ሳለ ወደ ‘ኢሜጅ ፕሮሰሲንግ’ መጠጋት ጀመርኩ።

ፎቶ ከወሰድሽ በኋላ ፎቶ ውስጥ የምትፈልጊውን አይነት መረጃ ለማግኘት በሂሳብ ወይም በሌላ አይነት ‘አልጎሪትም’ [በመጠቀም] ‘ፕሮሰስ’ ታደርጊያለሽ። ‘ሲማ ፕሮሰሲንግ’ የሚባል ዘርፍ ሳጠና ለ’ኮምፒውተር ቪዥን’ ፍላጎት አሳደርኩ። ‘ኮምፒውተር ቪዥን’ እየሰራሁ ሳለ ወደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ገባሁ።

ከጥናቶሽ መካከል ስለ ፌሽያል ሪኮግኒሽን ሲስተም (የሰዎችን ፊት ገጽታ በማየት ማንነታቸውን የሚያሳውቅ መተግበሪያ) የሰራሽው ይጠቀሳል። አሜሪካ ኑሮ ተሞክሮሽን የተመረኮዘ ነው?

ጥናቱን የጀመረችው ‘ኤምአይቲ ሚዲያ ላብ’ የምትሰራ ጆ የምትባል ጓደኛዬ ናት። ጥቁር ሴት ነች። ለአንድ ፕሮጀክት ‘ፌስ ሪኮግኒሽን’ ስትጠቀም ፊቷን ‘ዲቴክት’ ማድረግ [ማንበብ] አልቻለም። እንደሌለች ነው የሚቆጥረው. . . ነጭ ‘ማስክ’ [ጭንብል] ፊቷ ላይ ስታደርግ ግን ያነባል። ‘ፌስ ሪኮግኒሽን’ ነጮችና ጥቁሮች ላይ እኩል አይሰራም። ከጓደኛዬ ጋር የጻፍነው ጥናት የሚያሳየው በተለይ ጠቆር ያሉ ሴቶች ላይ በደንብ አለመስራቱን ነው።

ሌሎች ሰዎች [ጥቁር ያልሆኑ ተመራማሪዎች] ይህን ሳያጠኑ እኛ ያጠናነው ለምን እንደሚያስፈልግ ስለሚገባን ነው። አፍሪካውያን ‘የፌስ ሪኮግኒሽን’ ቴክኖሎጂ እኛ ጋርም ይሰራል ብለው ቢወስዱት አይሰራም። [ጥናቱ] ለራስሽ የሚጠቅም ቴክኖሎጂን ራስሽ መስራት እንዳለብሽ ያሳያል።

ወደ አፍሪካ የሚወሰዱ የፈጠራ ራዎችን ካነሳሽ አይቀር ሂደቱን እንዴት ታይዋለሽ?

ብዙ ቴክኖሎጂ ወደ አፍሪካ ይወሰዳል። አንድ የሰራሁት ጥናት፤ አሜሪካ ውስጥ መኪና ሲሰራ የአደጋ ተጋላጭነትን ለማጥናት የሚውለው አሻንጉሊት ላይ ያተኩራል። የሚጠቀሙት አሻንጉሊት የጎልማሳ ወንድ መልክ [ተክለ ሰውነት] ያለው ነበር። ታዲያ የመኪና አደጋ ሲደርስ ከሚሞቱት አብዛኞቹ ሴቶች ነበሩ። ችግሩ የመጣው አብዛኛው መኪና የተሞከረው ወንድ በሚመስል አሻንጉሊት ስለሆነ ነው። ይሄ ክፍተት የታየው [ክፍተቱ እንዳለ የታወቀው] ከ15 ዓመት በፊት ነበር።

ከዛም የሴቶች አይነት መልክ [ተክለ ሰውነት] ያላቸው አሻንጉሊቶች ለሙከራ ይዋሉ የሚል ህግ ወጣ። ብዙ ሴት ኢንጂነሮች [በሙከራው] ቢሳተፉ ኖሮ እነሱን የሚመስል ሰው ላይ የመኪና አደጋ ሲደርስ ምን ይሆናል? ብለው ይጠይቁ ነበር። መኪናው ሲሰራም ለወንዶች አደጋ የማያመጣ ብቻ ሳይሆን፤ ለሴቶችና ለልጆችም የሚሆን ይሆን ነበር።

መኪና ሲሞከር እዚህ ሀገር [የምዕራቡ ዓለም ሹፌሮች] እንዴት እንደሚነዱ እየታየ [እየተጠና] ነው። አፍሪካ ውስጥ ግን ዝም ብለን ሌላ ሀገር የተሰራ መኪና እያመጣን እንጠቀማለን። አሁን ደግሞ ራሱን የሚያሽከረክር መኪና እየመጣ ነው። ሌላ ቦታ ተሞክሮ ወደ አፍሪካ ሲመጣ እንዴት እንደሚሰራ አናውቅም። የአፍሪካ መንገድ ላይ እንዴት እንደሚሄድ አይታወቅም። ስለዚህ ሌላ ሰው [ለሌላ ሀገር] የሰራውን ቴክኖሎጂ ማምጣት አደገኛ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበሩ አብዛኞቹ ፈጠራዎችም አገር በቀል አይደሉም።

ይሄ በጣም ያሳዝነኛል። በኢትዮጵያ ጠረጴዛ እንኳን ባህላዊ አሰራር አለው። በጥበብ የሚሰራ. . . የሚያምር. . . ጥራት ያለው። ሁሉም ሰው እሱን ትቶ ከውጪ ያስመጣል። ሰው የራሱን ባህል ሳያከብር፤ በራሱ ባህል እንዴት አይነት ጥበብ እንዳለ ሳይስብ፤ ዝም ብሎ ውጪ የተሰራውን ለማምጣት ሲሞክር ለሀገሪቷም ጥሩ አይሆንም።

እኛ ምን መስራት እንችላለን? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። የኛው ሰው፤ ለኛ የሚሆን ነገር መስራት እንዲችል ማድረግ አለብን። ከውጪ ማምጣት ብቻ ከሆነ፤ ሀገር ውስጥ የሚሰራ አይኖርም። ለሀገሪቷ የሚጠቅማት ነገርም አይመጣም።

ትምኒት፣ ‘ዳታ አክቲቪስት (ዲጂታል መረጃን ያማከለ የመብት ተሟጋች) መሆንሽን እንዴት ነው የምትገልጭው?

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የመብት ተሟጋች ብለው የሚያስቡት ፖለቲካ ውስጥ የገባ ሰውን ብቻ ነው። ስለ ቴክኖሎጂ ሲያስቡ ስለ መብት ሙግት አያስቡም። ምክንያቱም ብዙዎች ስለ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንጂ አሰራር አያስቡም። ቴክኖሎጂ ግን ከመብት ሙግት ጋር የተያያዘ ነው። ለአብዛኛው ሰው የማይሰራ ቴክኖሎጂ ከሰራሽ ለሰው የማይሆን ነገር እየሰራሽ ነው ማለት ነው።

ኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያን ሴቶች ለራሳቸው የሚሆን ነገር እንዲሰራ ከፈለጉ ቴክኖሎጂ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው እንዲያውቁ እፈልጋለሁ። ኒውስዊክ ላይ ስለ ‘ጂኖሚክ ሪቮሊሽን’ [የዘር ቅንጣት ጥናት] ዘገባ አንብቤ ነበር። ‘ሂውማን ጂኖም’ [የሰዎች የዘር ቅንጣት] ጥናት ሲሰራ ከአፍሪካ የተጠቀሙት [የወሰዱት] ናሙና ከአንድ በመቶ በታች ነበር። ነገር ግን ዓለም ላይ ካለው የዘር ቅንጣት በበለጠ በጣም የተሰባጠረው የአፍሪካ ነው።

መድሀኒት ሲያጠኑ [ሲሰሩ] በአብዛኛው ጊዜ የአፍሪካውያንን የዘር ቅንጣት አያዩም። ለምሳሌ ለካንሰር መድሀኒት ሲሰራ ያደረጉትን ጥናት [ከአንድ በመቶ በታች ናሙና የተወሰደበትን] ከተከተለ መድሀኒቱ ለአብዛኛው አፍሪካውያን የማይሰራ ነው። ይሄንን እንደ ሰብአዊ መብት ጥሰት ነው የማየው። ‘ዳታ አክቲቪዝም’ ሳይሆን ‘ቴክኖሎጂ አክቲቪዝም’ ሲባል እንደዚህ አይነት ነጥቦች ይነሳሉ።

ትምኒት ገብሩImage copyrightTIMNIT GEBRU

 

አጭር የምስል መግለጫትምኒት ገብሩ

በልጅነትሽ ትወጅው የነበረውን ሙዚቃ ገፋሽበት ወይስ. . .

በህጻንነቴ ፒያኖ እጫወት ነበር። አሁንም እጫወታለሁ። በሙዚቃ ‘ሜጀር’ [ዋና ትምህርት] ባላደርግም ትምህርት ቤት እያለሁ የፒያኖ ትምህርት እወስድ ነበር። እለማመድም ነበር። አሁንም ጊዜ ሲኖረኝ እጫወታለሁ። እንደ ድሮው ግን አልዘፍንም. . .

ኢትዮጵያ ውስጥ የምታከናውኛቸው ፕሮጀክቶች እንዴት እየሄዱ ነው?

ክረምት ላይ ‘አዲስ ኮደር’ የሚል ስልጠና ነበረን። ጓደኛዬ ጂላኒ ኔልሰን የጀመረው ፕሮጀክት ነበር። መስከረም ላይ ባህር ዳር የአይሲቲ ኮንፈረንስ ነበር። ‘ብላክ ኢን ኤአይ’ የሚባል ተቋም አለን። ብዙ ጥቁሮች ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ውስጥ አይሳተፉም፤ ቢሳተፉም ሌላው ማህበረሰብ አያያቸውም።

ስለዚህ በኮንፈረንሶች ወይም ሌላም ቦታ የመሳተፍ እድል እንዲያገኙ እንሰራለን። ውስጡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። ታህሳስ ላይ ትልቅ ‘የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ኮንፈረንስ አለን። ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚሰሩትን ጥናት ለማቅረብ እንደሚመጡ ተስፋ አደርጋለሁ።

‘ብላክ ኢን ኤአይ’ ጥቁር ሴቶችን ተሳትፎ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከማሳደግ አንጻር ያመጣው ለውጥ አለ?

ከጀመርነው አንድ ዓመቱ ነው። በአንድ ዓመት ብዙ ለውጥ እንደመጣ አይቻለሁ። «ከዚህ ሙያ ልወጣ ነበር፤ ወደናንተ ተቋም ከመጣሁ በኋላ ግን ጥናት መስራት ጀምሬያለሁ’ ብለው ኢሜል ያደርጉልናል። ሥራ ያገኙ፤ ማስተርስና ፒኤችዲ ማጥናት የጀመሩም አሉ። በእኛ ወርክሾፕ ተገናኝተው በጥምረት መስራት የጀመሩም አሉ።

‘ዳታ ሳይንስ አፍሪካ’ የሚባል የምሥራቅ አፍሪካ ኮንፈረንስ አለ። ብዙ ጊዜ የሚካሄደው ኬንያ፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ግን ወደ ኢትዮጵያ ለመውሰድ እያሰቡ ነው። [ሁለንተናዊ] ለውጥ ለማምጣት ጊዜ ይወስዳል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮንፈረንሱ ስሄድ፤ ከ8,500 ሰዎች ስድስት ጥቁሮች ብቻ ነበሩ። አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ አሜሪካ. . . እንዳለ ተደምሮ ስድስት ሰው ብቻ! አስቢው? በጣም ትንሽ ሰው ነው። ባለፈው ዓመት ወርክሾፕ ላይ 200 ጥቁሮች ነበሩ። በዚህ ዓመት እስከ 500 ሰዎች እየጠበቅን ነው። ከ8,500 ጋር ሲነጻጸር [ቁጥሩ] ያን ያህል አይደለም። ስለዚህ በጣም ብዙ መስራት አለብን።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ወጣቶች በ’አርቴፍሻል ኢንተለጀንስዘርፍ ጅማሮ እያሳዩ ነው። ሆኖም የጎላ አይደለም። ዘርፉ እንዲጎለብት ምን መደረግ አለበት?

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን [አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ] እየታወቀ የመጣ ይመስለኛል። ችግሩ ኢትዮጰያ ውስጥ ጎበዝ የተባለው ሰው ባጠቃላይ ህክምና ማጥናት ነው የሚፈልገው። ሰዎች ወደ ቴክኖሎጂው እንዲገቡ እድል መስጠት አለብን።

የግል የቴክኖሎጂ ድርጅቶች መጀመር አለባቸው። ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ ብዙ የቴክኖሎጂ ተቋሞች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም መጀመር አለበት። እንደ አይስአዲስ ያሉ ድርጅቶች [መኖራቸው] በጣም ነው ደስ የሚለኝ። መንግሥት ራሱ እንደዚህ አይነት ነገር ማበረታታት አለበት።

ሰዎች የራሳቸውን [የቴክኖሎጂ] ድርጅት እንዲጀምሩ ወይም ትልልቅ [ዓለም አቀፍ] ድርጅቶች እንዲመጡ መደረግ አለበት። በኢትዮጵያውያን፤ ለኢትዮጵያ የሚሆን ተቋም [ቢበራከት] ጥሩ ነው። መንግሥት ገንዘብ የሚሰጠው የጥናት ተቋም ያስፈልጋል። የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎች በደንብ እየተከፈላቸው በትኩረት ጥናት እንዲሰሩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

ባለፈው ዓመት ባህር ዳር ውስጥ በተካሄደው የአይሲቲ ኮንፈረንስ ለ’አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ጊዜ ተሰጥቷል። ዘርፉ መታወቅ እየጀመረ ነው። ግን የተዋቀረ አካሄድ መኖር አለበት። ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት እቅድም መኖር አለበት።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስበአንዳንዶች እይታ የወደፊቱን ለም አስፈሪ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለምን የተሻለ ለማድረግ ተስፋ የሚጥሉበት አሉእነዚህ ሁለት ጽንፎች ባንቺ እንዴት ይታያሉ?

አንዳንዶች ማሽኖች ከሰዎች የበለጠ ሲያውቁ ሰውን ያጠፋሉ ይላሉ። አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ የሚሉ ሰዎች ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ውስጥ የሚሰሩ አይደሉም። ለምሳሌ ኢላን ማስክ እንዲህ ይላል። ግን የ’አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ባለሙያ አይደለም። ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች እንዲህ ሲሉ ያናድደኛል። አዲስ ፋሽን ሆኖ መጣ ስለተባለ ብቻ ስለሙያው የሚያወሩ ሰዎችም በጣም ያናድዱኛል።

‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ እንደ ሁሉም ቴክኖሎጂ ለጥሩም፤ ለመጥፎም መዋል ይችላል። ለምሳሌ አንድ ድርጅት የአልትራሳውንድ ማሽን ለመግዛት ብዙ ገንዘብ ያወጣል። በስልክ ላይ የሚሰካ በጣም ትንሽ የአልትራሳውንድ መሳሪያ ይህን ይቀርፋል።

በሌላ በኩል አሜሪካ ውስጥ ሰው ለመግደል ድሮን ይጠቀማሉ። የዚህ ተቃዋሚ ነኝ። ምክንያቱም ሁሉም ሰው በፍትሀዊ መንገድ ይፈረድበታል እንጂ ዝም ብሎ ሰው መግድል ያለብሽ አይመስለኝም። ይሄ የ’አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ችግር ሳይሆን የሰው አመለካከት፣ የፖሊሲ፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ ነው።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የዛሬ 100፣ 200. . . ዓመት ምን ሚና ይኖረዋል? ለወደፊት ምን አይነትለም ይታይሻል?

200 ዓመት ወደፊት ማየት አልችልም። ቴክኖሎጂ የሚገመት አይደለም። ምን አይነት እድገት እንደሚመጣ አናውቅም። ሌላው ነገር ቆሞ ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ብቻ ካደገ አንድ ነገር ይመጣል። ግን ቴክኖሎጂ ባጠቃላይ አንድ ላይ ነው የሚቀየረው። ለምሳሌ የጂን [የዘር ቅንጣት] ጥናት ብዙ አይነት ነው። ብዙ ነገር ሊቀየር ይችላል።

[በሌለ በኩል] ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ሁሉንም የምንሰራውን ሥራ ስለሚሰራ ሰዎች መስራት አይኖርባቸውም። ሰዎች ካልሰሩ እንዴት ገንዘብ ያገኛሉ? ‘ዩኒቨርሳል ቤዚክ ኢንካም’ [ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ ገቢ] መኖር አለበት የሚሉ አሉ።

በጣም የሚያሳስበኝ ‘ክላይሜት ቼንጅ’ [የአየር ንብረት ለውጥ] ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ሁላችንም ካልሞትን፣ ካልጠፋን [በአሁኑ እና በወደፊቱ ዓለም መካከል] ይሄን ያህል የተጋነነ የሆነ ልዩነት የሚኖር አይመስለኝም።

ቴክኖሎጂ ጥሩ ነገር ይሆናል ብዬ ሳስብ. . . አፍሪካ ውስጥ የድሮን ጥናት የሚሰሩ ጀማሪዎች አሉ። እናም መንገድ ሳያስፈልግ በድሮን መድሃኒት ማዳረስ ይቻል ይሆናል. . . ትልልቅ ሆስፒታል መስራት አያስፈልግ ይሆናል። በትንንሽ መሳሪያ ህክምና መስጠት ይቻልም ይሆናል።

ራሳቸውን የሚያሽከረክሩ መኪኖች ሲኖሩ አይነ ስውሮች በራሳቸው መንቀሳቀስ ይችላሉ። ሊሆንም፣ ላይሆንም ይችላል። ግን [ጥያቄው] ሰዎች እንዴት አድርገን ነው [ቴክኖሎጂን] የምንጠቀመው? ብዙ ጦርነት ይኖራል? ኢ-ፍትሀዊነት ይኖራል? በጣም ጥቂት ሰዎች ብዙ ገንዘብ ኖሯቸው ብዙዎች ገንዘብ ከሌላቸው ‘አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ያባብሰዋል።

ምን አይነት ፖለቲካዊ ሁኔታ ይኖረናል? ሰዎች እንዴት እብረን እንኖራለን? አካባቢያችንን እንጠብቃለን? [ጥያቄዎቹ ናቸው]። በአየር ንብረት ለውጥ መጀመሪያ የሚጠፉት ደሴቶች ናቸው። ከዛ በኋላ በጣም የሚጎዱት የመሬት ወገብ ላይ ያሉ ሀገሮች ናቸው።

የሚጎዱት እንደ ኢትዮጵያና እንደ ኬንያ. . . በአብዛኛው አፍሪካ ውስጥ ያሉት ሀገሮች ናቸው። ስለዚህ ጉዳይ እያሰብን አለመሆኑ ያሳዝነኛል። ቴክኖሎጂን ለምን መጠቀም ነው የምንፈልገው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከቻልን፤ በ’አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ’ ምን አይነት ኑሮ ይኖረናል የሚለውን ጥያቄ መመለስ እንችላለን።

ለ’አርቴፊሻል ኢንተለጀንስአቻ አማርኛ አግኝተሽለታል?

እኔ አላውቅም። ሰለሞን [የ ‘ቴክቶክስ’ አዘጋጅ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ] ሰው ሰራሽ ክህሎት ይለዋል።

ተስማማሽበት?

አዎ. . . ሌላ ምን ማለት ይቻላል? ክህሎት፣ ችሎታ ነው። ‘ኢንተለጀንስ’ን በአማርኛ ሲተረጎም ግን. . .

ለመሆኑ የምትወጂው በዓል የቱ ነው?

እ. . . እንቁጣጣሽ

እንቁጣጣሽ ከሌላው በል በምን ተለየ?

ሁሉም ነገር «በዓል ነው» ብሎ ይነግርሻል። አደይ አበባው. . . አየሩ. . . [ዘመን] እየተለወጠ እንደሆነ ይነግርሻል። ሆያ ሆዬ ሲጨፈር ራሱ. . . ጭፈራ ደስ ይለኛል።

ልን ከኢትዮጵያ ውጪ እንዴት ታሳልፊያለሽ?

ከጓደኞቼ ጋር ተገናኝቼ ‘ዘኒ’ የሚባል የኢትዮጵያ ሬስቶራንት እንሄዳለን። እንበላለን፤ እንጠጣለን። ቡና ማፍላት አልችልም. . . መማር አለብኝ። እና ጓደኞቼ ቡና ያፈላሉ። እናቴና ቤተሰብ ቤት መሄድ ከቻልኩ እሄዳለሁ። እነሱ የሚኖሩት ቦስተን ነው። እናቴ ቆንጆ ላዛኛ ትሰራለች። ቀይ ወጥ፣ ዶሮ ወጥ ሰርታ አብረን እናሳልፋለን።

የምትወው ምግብና መጠጥ ምንድን ነው?

ሽሮ በጥቅል ጎመን እወዳለሁ፤ [እየሳቀች] ሽሮ «የሞጃ ምግብ አይደልም ቢባልም» እወደዋለሁ። ጣፋጭ በተለይም ቸኮሌት እወዳለሁ። ቡና በወተት እወዳለሁ። ሁሌ ጠዋት ስነሳ ቡና በወተት እጠጣለሁ።

የምታዘወትሪው የቴሌቭዥን ዝግጅትስ?

‘ብሮድ ሲቲ’ የተባለውን ተከታታይ ፊልምና ‘ደይሊ ሾው ዊዝ ትሬቨር ኖሀ’ እወዳቸዋለሁ። ቴክ ቶክና ሄለን ሾው ቃለ መጠይቅ ካደረጉኝ በኋላ እከታተላቸዋለሁ።

ያንቺ ምርጡ መጽሐፍ የቱ ነው?

ከሥራዬ ጋር የሚገናኙት ላይ አተኩራለሁ። ‘ዌፐንስ ኦፍ ማት ዲስታራክሽን’ የምወደው መጽሐፍ ነው።

የምትወጂው ሙዚቃስ?

ከአዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ሙሉ ቀን የማዳምጠው የሮፍናን አልበምን [ነጸብራቅ] ነው።

የምታዘወትሪው ድረ ገጽ አለ?

ፌስቡክና ትዊተር እንዳሉ ሆነው፣ ‘ስታክ ኦቨር ፍሎ’፣ ‘ሬድዮ ላቭ ፖድካስት’ እና ‘አፍሪካ ኢዝ ኤ ካንትሪ’ የተባሉትን እከታተላለሁ።

የሚያስደንቅሽ ሳይንሳዊ ፈጠራ ምንድን ነው?

[እንደ ሳይንስ ሙያተኛነቷ አንዱን መምረጥ አስቸጋሪ መሆኑን ካስረዳች በኋላ] ቴክኖሎጂ ጥሩ የሚሆነው በሰው አመለካከት ልክ ነው። ለምሳሌ ተንቀሳቃሽ ስልክ በእጅ ተይዞ ስንት ነገር እንደሚሰራ ሲታሰብ ያስደንቃል።

የምታደንቂው ሳይንቲስትስ?

አብዛኞቹ የማከብራቸው ሳይንቲስቶች ሳይሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ናቸው። የማደንቃቸው ሰዎች በማህበረሰባቸው ውስጥ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ናቸው። ሜሪ ኪዩሪ ሁለት ጊዜ ኖቤል ሽልማት አግኝታለች። መጀመሪያ ለሷ ሊሰጧት አልፈለጉም። ለባሏ መስጠት ነበር የፈለጉት። ባሏ ግን ከሷ ጋር ካልተካፈልኩኝ መውሰድ አልፈልግም አለ።

መጀመሪያ የተመራመረችው እሷ እንደሆነች ያውቅ ነበር። ወንዶች ለሴቶች መታገል አለባቸው። ሴቶች ብቻችንን ይህንን ትግል ማሸነፍ አንችልም። በሳይንስ ውስጥ አሁን ያለውን ኢ-ፍትሀዊነት ሳስብ፤ በሷ ጊዜ ደግሞ ምን [ያህል ከባድ] ነበር ብዬ አስባለሁ። በዚያ መድልዎ ሁለት ኖቤል ሽልማት ማግኘቷ ያስገርመኛል።

የምትወጂው አባባል አለ?

አለ፤ ‘just do it’! በአማርኛ ሲተረጎም ‘ይቻላል’ ቢባልም እንደ እንግሊዘኛው አይሆንም። ሰዎች አስሬ እንዲህ ባረግ ከማለት ማድረግ አለባቸው። ሰዎች አቅማቸውን አያውቁም። የይቻላል መንፈስ ካላቸው ግን ያደርጉታል።

ምን አይነት አለባበስ ያስደስትሻል?

ሽሮ ሜዳ የሚሸጡትን ምቹ የሀበሻ ልብሶች እወዳቸዋለሁ።

ከጎበኘሻቸው ቦታዎች የማትረሽው የቱን ነው?

የኬንያን ላሙ አልረሳውም። ቦታው የሚያምር፣ ሰዎቹም ደስ የሚሉ ናቸው። ኩባም የማይረሳኝ ቦታ ነው።

ለወደፊትስ የት መሄድ ትፈልጊያለሽ?

ሞዛምቢክ፣ ባህር ዳርቻ።

የትምኒት መደበኛ ቀን ምን ይመስላል?

[እየሳቀች] እንቅልፍ እወዳለሁ። ከስምንት እስከ አስር ሰአት በደንብ እተኛለሁ. . . ስነሳ ቡና በወተት እጠጣለሁ. . . ውሾች እመግባለሁ. . . ኢሜል አደርጋለሁ. . . ጠዋት ላይ አነባለሁ፣ ሙያውም ብዙ ማንበብ ስለሚጠይቅ ጥናትና ምርምሮች አነባለሁ. . . እሮጣለሁ. . . ዮጋ እሰራለሁ. . . ከጓደኖቼ ጋር ምሳ እበላለሁ. . . [እየሳቀች] ጊዜ ማጥፋት በደንብ እችላሉ. . . ዘፈን እየሰማሁ፣ ልብስ እያጠብኩ ሶስት አራት ሰአት ይሄዳል። ከዛ እራት ይበላል. . .

ምንጭ: BBC

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.