“ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለብቻዬ ሰራኋት ሊል አይችልም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ንግግር ሲያደርጉ

‘ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና’ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የኢህአዴግ ጉባዔ ላይ የግንባሩ አባል ድርጅቶች አመራሮችና አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የወዳጅ ሀገራት ልዑካን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ንቅናቄ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል የጉባኤውን ታዳሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ጉባዔውን በንግግር አስጀምረዋል።

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጋብዘዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በንግግራቸው ጉባዔው የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል የሚወስን እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢህአዴግ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሳይንሳዊ መፍትሄ በመስጠት እንደፈታ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ወቅታዊ ለውጥ የምናካሄደው የህዝቡን ደጀንነት በመያዝ በኢህአዴግ መሪነት ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አብሪ ኮከብ ለመሆን እየተጋች ነች በማለት ተናግረዋል።

በንግግራቸው ሀገር የምታድገው በቅብብሎሽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲሱ ትውልድ ከማማረር ይልቅ ያለፈውን ትውልድ በማመስገን ከቀደመው ትውልድ በጎ በጎውን በመውሰድ መማር ያስፈልገዋል ብለዋል።

“የአዲሱ ትውልድ ተተኪ መሪዎችም ያለፈውን ነገር ሁሉ ማማረርና ባለፈው ትውልድ ላይ ማሳበብ አይገባቸውም። ይልቅም ያለትናንት ዛሬ አልተገኘምና ያለፈውን ትውልድ ማመስገን ያስፈልጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚደረገው ሽግግር በመመሰጋገን እና በመተራረም ላይ የሚያደርግ የፖለቲካ ባህል መትከል ያስፈልጋል። መተካካት የታቀደ የፖለቲካ ባህል እንጂ ድንገተኛ የመበላላት ክስተት እንዳይሆን ስርዓት መትከል ያስፈልጋል ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ተተኪ የማያፈራ መሪ እንደማይባል ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትውልዱ ቀድሞ የነበረውን በማፍረስ ላይ መጠመድ እንደማያስፈልግ “እጅና እጅ ሆነን ከፍታችንን መውጣት ይገባናል” ሲሉ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አምባገነን መሪዎች እንደነበሯት ሁሉ ለሀገር አንድነት የሰሩ መኖራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “በአሁኑ ወቅት ያሉት አመራሮችስ? ኢትዮጵያን የዓለም ራስ እናደርጋታለን ወይስ ጭራ?” በማለት ለተሰብሳቢው ጥያቄ አቅርበዋል።

መሪነትን በፖለቲካ እና በመንግሥት ስልጣን ላይ ፊጥ ማለት አድርጎ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ህዝብን የሉዓላዊ ስልጣን ምንጭ አድርጎ ማሰብ ተገቢ ነው ብለዋል።

Image copyright EBC

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በንግግራቸው ሀገር የተሳካ ጉዞ መጓዝ የምትችለው ሕዝብ የሚያዳምጣቸውና የሚከተላቸው የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሞራልና የግብረገብ መሪዎች በብዛት ሲገኙ፤ የማህበረሰብን የአስተሳሰብ ደርዝ የሚያሰፉ፣ በሀሳብ ልዕልና የሚያምኑ፣ ትውልድን የሚቀርፁ የእውቀትና የፍልስፍና ልሂቃን ሲበራከቱ ነው ብለዋል።

በስራና ሀብት ፈጠራ የተካኑ፣ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ የብልፅግና ቁመና ያላቸው፣ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሾች ካሉና ጎልተው ከወጡ፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምርና ጥናት ዓለም ከደረሰበት የእድገት ማማ ላይ በፈጣን ግስጋሴ የሚያደርሱ ታላላቅ ተመራማሪዎችና መምህራን በየዩኒቨርስቲዎቹ ከተገኙ እንደሆነም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ግጭትና ሽብር በበዛበት ዓለም ላይ ለልዑላዊነታችን መከበርና ለሰላማችን መረጋገጥ በሰለጠነ መልኩ ስልጡን የጦር መሪዎች ቦታቸውን ከያዙ፣ በሙያዊ ክህሎታቸውና በአመለካከታቸው የበሰሉ የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሱ በተለያዩ የስራ መስኮች ከተሰማሩ እንደሆነም በዝርዝር አስረድተዋል።

“የተረከብናትን ኢትዮጵያ አለመውደድ መብታችን ነው፤ የምናስረክባትን ኢትዮጵያ ግን አስውበን ማስረከብ ግዴታችን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እኛን ልትመስል የተዘጋጀች ነች ብለዋል።

የ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ አርማImage copyrightEPRDF FB
አጭር የምስል መግለጫየ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ አርማ

“ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለብቻዬ ሰራኋት ሊል አይቻለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በሁላችንም ላብና ደም የተሰራች በመሆኗ የጋራችን ናት ብለዋል። በመሆኑም ኢህአዴግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ድርጅት እንዲሆን ጉባዔው የተለየ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም በንግግራቸው ገልፀዋል።

አክለውም “በዋናነት ፉክክራችን ከዓለም ጋር እንጂ እርስ በእርሳችን ሊሆን አይገባም፤ ከዓለምም ጋር ስንፎካከር በመጠፋፋት መንፈስ ሳይሆን ለሁላችንም የምትሆን የተሻለች ዓለምን በመገንባት መንፈስ ላይ መሆን ይኖርበታል” ብለዋል።

የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ለሶስት ቀናት በተለያየ ጉዳይ ላይ በመምከር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.