እውነተኛውን ምስል ከሐሰተኛ ለመለየት የሚረዱ ዘዴዎች

በማህበራዊ ሚዲያው ሁሉም የራሱን ሃሳብ ይሰጣል። መረጃዎችን ያሰራጫል። የመረጃው እውነት ወይም ሃሰት መሆኑን የመለየቱ ፈንታ ግን የተጠቃሚው ነው።

ሐሰተኛ ዜና ወይም ‘ፌክ ኒውስ’ የማሕበራዊው ሚዲያ ተጠቃሚዎች ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል።

ሐሰተኛ ዜና ሆነ ተብሎ የፖለቲካ ወይም የገንዘብ ፈላጎትን ለማሟላት የሚሰራጭ ሐሰተኛ መረጃ ማለት ነው። ስለዚህ በርካቶች የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ሃሰተኛ መረጃዎችን እውነት በማስመሰል ያሰራጫሉ።

የአንድን ፎቶ ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል ይዘትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚረዱ በርካታ መንገዶች አሉ። እነዚህን ዘዴዎች ከመተግበራችን በፊት የመጀመሪያው ተግባር መሆን ያለበት ግን ፎቶግራፉን ወይም ተንቀሳቃሽ ምስሉን በአትኩሮት መመልከት ይቀድማል። በምስሉ ላይ የሚታዩ ጥቃቅን ነገሮችን በአትኩሮት ማየት ትልቁን እውነታ እንድንረዳ ይጠቅመናል።

ለምሳሌ አንድ አጠራጣሪ ፎቶ ወይም ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስንመለከት፤ በመጀመሪያ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ምን እንደሆነ እራሳችንን እንጠይቅ።

ከዚያም ፎቶግራፉ ወይም ቪዲዮ ኤዲት ተደርጎ እንደሆነ ማስተዋል። ምስሉ የተነሳበትን አካባቢ፣ በምስሉ ላይ ያሉ ልዩ ምልክቶች፣ ፎቶ በተነሳበት ወቅት የፀሐይ ብርሃን አቅጣጫን ወዴት እንደሆነ እና በምስሉ ላይ የሚታዩ ሰዎች ወይም የቁሶችን ጥላ በአትኩሮት መመልከት ያስፈልጋል።

በዚህም እነዚህን ምስሎች ያሰራጩት ሰዎች ከምስሎቹ ላይ እንድንመለከት ከተፈለገው ነገር ባሻገር ሊሰጠን የሚችል ትርጉም ካለ በጥንቃቄ መፈተሽ ይኖርብናል።

ከዚህ ቀጥሎ የሚከተሉትን መንገዶችን በመጠቀም እውነትን ከውሸት መለየት ይቻለናል።

1.ጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ (Google Reverse Image)

ጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ የምንሰጠውን ምስል በመጠቀም ከሰጠነው ምስል ጋር ተቀራራቢ ወይም እንድ አይነት ምስሎችን ያሳየናል።

ጉግል ኢሜጅ ሰርች (Google Image Search) ብልን ጉግል ብናደርግ ወደ ጎግል ኢሜጅ (Google Image) ገጽ ይወስደናል። ከዚያም ማረጋገጥ የምንፈልገውን ፎቶግራፍ ከኮምፒዩተራችን ወይም የኢንተርኔት አድራሻውን እንድናስገባ ይጠይቀናል።

ይህን ካደረግን በኋላ ጉግል ከሰጠነው ምስል ጋር የሚቀራረብ ወይም የሰጠነው ምስል ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ከዋለ ማወቅ ያስችለናል።

ተንቀሳቃሽ ምስል ከሆን ደግሞ ከምስሉ ላይ አንድ ፍሬም ስክሪን ካፕቸር በመውሰድ በተመሳሰይ መልኩ ማጣራት እንችላለን።

2.ቲንአይ (TinEye)

ቲንአይ ጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ የሚጠቀመውን አይነት ቅደም ተከተሎችን በመጠቀም ምስሉን ካስገባን ከሰጠነው ምስል ጋር ተቀራራቢ ወይም ተመሳሳይ ምስል አፈላልጎ ያቀርብልናል።

ከዚህ ቀደም በርካቶች ከኢትዮጵያ ውጪ የተነሱ ፎቶግራፎች በሃገር ውስጥ የሆኑ በማስመሰል ያቀረቧቸው ምስሎች ሐሰት መሆናቸው በዚህ ቴክኒክ አማካኝነት ማረጋገጥ ተችሏል።

3.ፎቶፎረንሲክስ (Fotoforensics)

ፎቶፎርነሲክስ (Fotoforensics) ነጻ እና ለአጠቃቀም ቀላል የሆነ ደረ-ገጽ ሲሆን፤ ፎቶግራፎችን በመጫን ወይም የኢንተርኔት አድራሻ በማስገባት ምስሉ ኤዲት መደረጉን ወይም አለመደረጉን ማወቅ ያስችላል።

ፎቶፎርነሲክስ ኢረር ሌቭል አናሊሲስ (Error Level Analysis) የሚባል ቴክኒክን በመጠቀም አንድ ፎቶ በሶፍትዌሮች አማካኝነት እንዲቀየር ከተደረገ መጠቆም ያስችላል።

ወደ fotoforensics.com በመሄድ አንድን ምስል ከጫኑ በኋላ፤ የጫኑት ምስል ስር የዚያው ምስል ግልባጭ በጥቁር ገጽ ላይ ሆኖ ይታያል። ።

በጥቁሩ ምስል ውስጥ ቀይ ወይም ነጭ የሆኑ ቦታዎች በፎቶው ላይ ይሚታዩ ከሆነ፤ ቀዩ ወይም ነጩ ቀለም ያረፈበት ቦታ ኤዲት የተደረገ የምስሉ ክፍል መሆኑን ይጠቁማል።

አይሸወዱ፡ እውነቱን ከሐሰት ይለዩ

4.ፎቶግራፍ የተነሳበትን ቦታ ማወቅ

ዘመናዊ የሚባሉ ስልኮች የተገጠመላቸው ካሜራ ፎቶግራፍ ሲያነሳ ቦታውን እንዲመዘግብ የተፈቀደለት ከሆነ ፎቶግራፉ የተነሳበትን ቦታ ማወቅ ይቻለናል።

የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ ወደ ስልኩ መቼት ሄዶ ሎኬሽን ሰርቪስ (location service) የሚለውን አገልግሎት ካሜራው እንዳይጠቀም ካልከለከለው በስተቀር የሚነሱትን ፎቶግራፎች አድራሻ ማወቅ ይቻላል።

ፎቶግራፉን በኮምፒዩተራችን ላይ ካስቀመጥን በኋላ ራይት ክሊክ (right click) በማድረግ ፕሮፕርቲስ (properties) የሚለውን መጫን። ከዚያም ዲቴይልስ (details) የሚለወን ከተጫንን በኋላ ጂፒኤስ (GPS) ከሚለው ስር የሚገኙትን longitude እና latitude አድራሻዎችን ወደ ጉግል ማፕ በመውሰድ ፎቶግራፉ የተነሳበትን ቦታ ማወቅ ይቻለናል።

5.ዎችፍሬምባይፍሬም (Watchframebyframe)

በሶፍትዌሮች አማካኝነት የሚቀነባበሩ ሃሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በጥልቅ በመመልከት ሐሰተኛ መሆናቸውን እንድናውቅ ይረዳናል።

በአንድ ሰከንድ ቪዲዮ ውስጥ እሰከ 24 ፍሬሞች (ፎቶግራቾች) አሉ። Watchframebyframe.com ላይ ተንቀሳቃሽ ምስሉን በመጫን ወይም የኢንተርኔት አድራሻውን በማስገባት ቪዲዮውን በዝርዝር በማየት ሆን ተብሎ ሰዎችን ለማሳሳት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የሚፈጠሩ ስህተቶችን ማግኘት ይቻላል።

እነዚህ መንገዶች ሃሰተኛ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን ለመለየት ከሚያስችሉ የተወሰኑትና ወጪን የማይጠይቁ መንገዶች ናቸው። ስለዚህም በየትኛውም መንገድ የሚሰራጩ ምስሎችን አምነን ከመቀበላችን በፊት በእራሳችን መንገድ ቀላል ማጣራት በመድረግ እራሳችንን ከሃሰተኛ መረጃ መጠበቅ እንችላለን።

በተጨማሪም ለሃሰተኛ መረጃ መስፋፋት ዋነኛው መንገድ ሳናጠራ ለሌሎች እንዲደርስ ማድረግ ይጠቀሳል። በዚህ መንገድ የምናስተላልፈው መረጃ እኛንም አሳስቶ ለሌሎችንም የሚያሳስት ከመሆኑም በላይ የእኛንም ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይጥላል።

ስለዚህ አጠራጣሪና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ተቀብለን ለሌሎች ከማጋራታችን በፊት በተጠቀሱት ቀላል የማጠሪያ መንገዶች በመጠቀም እራሳችንና ሌሎችን ከሃተኛ መረጃ መጠበቅ እንችላለን።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.