አውሮፓ በኩፍኝ ተቸገረች፡፡

በኪሩቤል ተሾመ

በአውሮፓ አህጉር በኩፍኝ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2018 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከ41 ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ፤37ቱ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡

ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት 23 ሺ927 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተመዝገበ ሲሆን ቀደም ባለው ዓመት ቁጥሩ 5ሺ273 እንደነበር ማወቅ ተችሏል፡፡
ለበሽታው መባባስ ዋናው ምክንያት የተከተቡ ሰዎች አሀዝ መውረድ እንደሆነ ባለሙያዎች ይተቻሉ፡፡

በሽታው ወደተቀሰቀሰባቸው የአውሮፓ ሀገራት ዜጎቹ በመንቀሳቀሳቸው በሽታው በእንግሊዝ እንዲከሰት አድርጓል ሲል ፐብሊክ ሀልዝ ኢንግላንድ ገልጿል፡፡በዚህ አመት በእንግሊዝ 807 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡
በዚህም የተነሳ የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ሀገራት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ እያቀረበ ነው፡፡

ኩፍኝ በሳል እና በማስነጠስ ይተላለፋል ፤ ህመሙ ከሰባት እስከ አስር ቀናትም ይዘልቃል፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ቢያገግሙም በሰውነታቸው ላይ ውስብስብ ችግሮችን ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡ ለአብነትም ማጅራት ገትር ፣የመተንፈሻ አካል ችግር እና ሄፕታይቲስ ይጠቀሳሉ፡፡

ኤም ኤም አር ክትባት በሽታውን ይከላከላል ቢባልም ከ20 አመታት በፊት በተካሄደ ምርምር መድሃኒቱ ከአዕምሮ እድገት ውሱንነት ( ኦቲዝም ) ጋር በተገናኘ አጋላጭ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ አንዳንዶችም በክትባቱ ላይ የነበራቸውን አመኔታ መቀነሳቸውንም እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ሁሉም ህፃናት ሲወለዱ እና ት/ቤት ከመግባታቸው በፊት ክትባቱን እንዲወስዱ ይመክራል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅቱ ዶ/ር ኔርዲት ኢምሮግሉ እንዳሉት የመከላከል አቅሙ ዝቅተኛ የሆነ ሰው በየትኛውም ቦታ ይኑር ለበሽታው ተጋላጭ ስለሆነ እያንዳንዱ ሀገር በመከላከል በኩል ያለውን ክፍተት በመሙላት እና የጤና ሽፋኑን በማሣደግ ወረርሽኙን መቀነስ አለበት ብለዋል፡፡

ዩክሬን እና ሰርቢያ በሽታው ክፉኛ በትሩን ያሳረፈባቸው የአውሮፓ ሀገራት ናቸው፡፡

የኩፍኝ በሽታ ትኩሳት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የድካም ስሜት፣ የአይን መቅላት ወዘተ ከምልክቶቹ ውስጥ እንደሚጠቀሱ ባለሙያዎችን ያነጋገረው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ምንጭ:  Amhara Mass Media Agency

 

Advertisement

9 Comments

Comments are closed.