New Remedy for Migraines | ከባዱ የራስ ምታት ማይግሬን መድሃኒት ሊገኝለት ነው

ማይግሬን (በጭንቅላት የተወሰነ ከፍል ላይ የሚያጋትም የራስ ምታት) ከአምስት ሴቶች አንዷን የሚያጠቃ ሲሆን፤ ሥራን ጨምሮ አጠቃላይ የእለት ከእለት ህይወትን በከፍተኛ ሁኔታ ያውካል። ሆኖም በህመሙ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች በጣም ጥቂት ናቸው። በቂ የገንዘብ ድጋፍም አላገኙም።

ለመጀመሪያ ጊዜ የማይግሬን ህመም ያጋጠመኝ ከትምህርት ቤት ስመለስ ነበር ትላለች የቢቢሲ ጋዜጠኛ ላውረን ሻርኪይ። በመጠኑ ምቾት በመንሳት የጀመረው ህመም ቀስ በቀስ ወደ ከፍተኛ የራስ ምታት ተቀይሮ መፈጠረን የሚያስጠላ ህመም እንደሆነባት ትናገራለች።

”በማይግሬን ምክንያት ማንም ሰው ሊረዳኝ እንደማይችል እስከማሰብና እንደውም ሥራዬንም እስከመተውም ደርሼ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለዓመታት ኖሬያለሁ” ትላለች።

እስካሁን ድረስ የማይግሬን ትክክለኛ መንስኤ አልታወቀም። ሀኪሞችም የማያዳግም ህክምና መስጠት አልቻሉም።

የዓለም የጤና ድርጅት ከ195 ሀገራት በሰበሰበው መረጃ መሰረት እንደ አውሮፓውያኑ ከ1990 እስከ 2016 ድረስ ማይግሬን ሰዎችን ለአካል ጉዳት ከሚያጋልጡ በሽታዎች ሁለተኛውን ቦታ ይዟል።

ማይግሬን በዓለም ላይ ውስን ጥናት ከተደረገባቸው የጤና እክሎች አንዱ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ሴቶችን ያጠቃል። ከአምስት ሴቶች አንዷ በማይግሬን የምትጠቃ ሲሆን በአንጻሩ ከ15 ወንዶች አንዱ ብቻ ማይግሬን ሊይዘው ይችላል።

ሴቶች ላይ ለምን በብዛት የይከሰታል?

ማይግሬን በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይበት ምክንያት እስካሁን አይታወቅም።

የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ አይጦችን በመጠቀም በሰራው ጥናት መሰረት ልዩነቱ የተፈጠረው፤ ሴት አይጦች ”ኤን ኤች ኢ 1” የተባለ ንጥረ ነገር በሰውነታቸው ውስጥ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ስላለና ወንድ አይጦች ደግሞ ”ኤስትሮጂን” የተባለ ንጥረ ነገር በሰውነታቸው ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚገኝ ሳይሆን እንደማይቀር ጠቁሟል።

”ኤን ኤች ኢ 1” የተባለው ንጥረ ነገር ሰውነታችን ውስጥ በበቂ ሁኔታ ካልተገኘ ህመምን የመቋቋም አቅማችን በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል።

ማይግሬን በዋነኛነት ሴቶችን ቢያጠቃም በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ከተሰራው ጥናት ውጪ የተሰሩ ሌሎች ጥናቶች አብዛኛውን ናሙና የወሰዱት ከወንዶች ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 በተሰራ ጥናት ማይግሬን ካለባቸው ሰዎች ከሌለባቸው ጋር ሲነጻጸሩ በሦስት እጥፍ ለጭንቀት ይጋለጣሉ። ድብርት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በሦስት እጥፍ ለማይግሬን የተጋለጡ ናቸው።

በጥናቱ መሰረት በማይግሬን ከተጠቁ ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ ራሱን ለማጥፋት ያስባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ማይግሬን ለብዙ የአእምሮ በሽታዎች የሚያጋልጥ ቢሆንም እስካሁን አስተማማኝ ህክምና ሊገኝለት አልቻለም።

መፍትሄ ይገኝለት ይሆን?

ስለማይግሬን ሲያጠኑ የነበሩ ተመራማሪዎች በቅርቡ ተስፋ ሰጪ መድሃኒት ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። መድሃኒቱ ”ኢረንማብ” ይሰኛል። በመርፌ መልክ የሚወሰድ ይሆናል። መድሃኒቱ በወር አንዴ ይሰጣል። የማይግሬን በሽታ ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ ለመከላከል ይረዳልም ተብሏል።

መድሃኒቱን ለየት የሚያደርገው ከሌሎች በሽታዎች ጋር በተያያዘ ሳይሆን ለማይግሬን ብቻ ተብሎ መሰራቱ ነው። በማይግሬን የሚሰቃዩ ሰዎች በቅርቡ መፍትሄ ሊያገኙም ይመስላል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.