NEWS: ሳዑዲ በካናዳ የሚማሩ 15 ሺህ ዜጎቿ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

ሳዑዲ አረቢያ በካናዳ በትምህርት ላይ የሚገኙ 15 ሺህ የሚደርሱ ዜጎቿ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟን አስታወቀች፡፡

ሳዑዲ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ወደ እስር ቤት ማስገባቷን ተከትሎ ካናዳ ይህንን ድርጊቷን በመኮነኗ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከሰኞ ጀምሮ ማቋረጡ ይታወሳል፡፡

ሳዑዲ በሀገርዋ የሚገኙትን የካናዳ አምባሳደር ያስወጣች ሲሆን በኦታዋ ያሉትን አምባሳደርዋን ደግሞ አስጠርታለች፡፡

የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ከሆነ በካናዳ የሚገኙ የሳዑዲ ዜግነት ያላቸው ህሙማን ወደ ሦስተኛ ሀገር ሄደው በሚታከሙበት ጉዳይ ላይ የጋራ ትብብር እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡

ይህ ሁሉ ውዝግብ የመጣው የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ላይ ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን መያዝ አውግዞ ሳዑዲ በቶሎ እንድትለቃቸው ማሳሰቡን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

ወደ እስር ቤት ከገቡት ከሁለቱ ሴቶች መካከል አንደኛዋ የካናዳ ዜግነት ያላት መሆኑ ተነግሮዋል፡፡

እስከአሁን ሳዑዲ የንግድ ልውውጦችን፣ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንዲሁም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን አቋርጣለች፡፡

የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቲይ ፍሪላንድ በምላሻቸው ሀገራቸው በዓለም ዙሪያና በካናዳ ለሰብዓዊ መብት መከበር ሁሌም በጽናት እንደምትቆም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ግብጽ የካናዳን በሌላ ሀገር ጣልቃ መግባት በመቃወም ከሳዑዲ ጎን እንደምትቆም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርዋ በኩል አስታውቃለች፡፡

የሁለቱም ሀገራት ወዳጅ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ሀገራቱ የሻከረውን ግንኙነታቸው ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት አለባቸው ብለዋል፡፡

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.