በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ ከተሰባሰቡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በአሜሪካ ሁለተኛው በሆነው ህዝባዊ መድረክ ላይ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮያዊያን ተካፋይ ሆነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፈው ዘመን ኢትዮጵያዊያን ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ጊዜ ነበር ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ኢትዮጵያ ስም ካላቸው የአለም አገር ተርታ ለማሰለፍ እልህ አስጨራሽና ሁሉን አቀፍ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን በድህነት አረንቋ ውስጥ ያለውን ወገናችሁን ለመታደግ ልትደርሱላት ይገባልም ሲሉ ተማፅነዋል፡፡

በተለይም መሰረተ ልማት ያልደረሰባቸው አካባቢዎችን መርዳት፣ የትምህርትና መሰል ማህበራዊ ተቋማትን ያላገኙ ወገኖችን ልትደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡

አንድነትና በመተባባር የሚያስፈልገው አገሪቱን ካለችበት ድህንት ለማውጣት ብቻ ሳይሆን ከገጠማት ብልሹ አሰራርና ሙስና ለማፅዳት ጭምር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በርካታ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ባሉበት አገር ከዚህ በፊት የነበረውን የስልጣን ቆይታ ባልተለመደ ሁኔታ የአንድ መሪ የስልጣን ጊዜን በመቀየር ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳይሆን ይደረጋልም ብለዋል፡፡

የፕሬስ ነፃነት የተረጋገጠባት፣ ከሙስና የፀዳች አገር ለመፍጠር የጋራ መተባበርና ርብርብ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ለዚህም በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊ ድርሻው የጎላ መሆኑ አመልክተዋል፡፡

በእውቀታችሁና በገንዘባችሁም ወደ ኢትዮጵያ ገብታችሁ የጎደለውን የአገራችሁን ጓዷ በመሙላት የተበላሸውን እናስተካክል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ከአሁን ወዲህ መለያየቱ ቀርቶ ኢትዮጵያን የተከበረች አገር ለማድረግ መተባበር ይገባል ብለዋል፡፡በእውቀት ላይ የተመሰረተ የአገር አመራርና ግንባታም እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን እውቀትና ሀብት ይዘው ወደ አገራቸው እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዕለቱ የኢትዮጵያዊያን ቀን ሆኖ እንዲከበር የሎስአንጀለስ ከተማ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ምንጭ: EBC
Video source: ESAT TV

Advertisement