“የእሱ አባት ኩራዝ የላቸውም፤ እሱ ግን ኢትዯጵያን ሊያበራ ነው የሞተው”

ትናንት ባልታወቀ ሁኔታ መኪናቸው ውስጥ ህይወታቸው አልፎ የተገኘው የኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦች መሪር ሃዘን ውስጥ ናቸው። የቢቢሲ ዘጋቢ ትናንት የአስክሬን ምርመራ በሚካሄድበት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተገኝታ በጥልቅ ሐዘን ላይ የሚገኙ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን አነጋግራለች።

የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቤተሰብ አባላት ሐዘናቸውና ቅሬታቸውን በለቅሶ መሐል ሆነውም አጋርተዋታል።

የቅርብ ዘመድ ቢኾኑም ስለ ግድያው በሚዲያ መስማታቸውን የገለጹት እኒህ የቤተሰብ አባላት አስክሬኑ መጉላላቱና የሚገባውን ክብር አለማግኘቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ደግሞ አንድም የመንግሥት አካል በአካባቢው አለመኖሩ የፈጠረባቸውን ቅሬታንም አልሸሸጉም።

• ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሕይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመተው ነው፡ ፌደራል ፖሊስ

• ስለኢንጂነር ስመኘው አሟሟት እስካሁን ምን እናውቃለን?

“ቢሮ ተቀምጦ አይደለም መግለጫ መስጠት” ሲሉ የመንግሥት አካላት ላይ ያነጣጠረ የሚመስል ቅሬታን አሰምተዋል።

“እሱ ቤቱን ትቶ በረሀ ላይ ነው የኖረው። ለስመኝ ይሄ አይገባውም። ምን አረጋቸው፣ የበደላቸውን ለምን አይነግሩንም? ምን አደረጋቸው? ይሄ ለሱ አይገባውም” ስትል በመሪር ሐዘን ሆና ስሟን ያልገለፀች አንድ የቤተሰብ አባል ተናግራለች።

“ማነው ጀግና፣ ማነው ጎበዝ? ማነው ለአገር አሳቢ። የሚመስል ወይስ የሆነ?” ሲል በምሬት ሐዘኑን የገለጸው ሌላ ወጣት “የእሱ አባት ኩራዝ የላቸውም፤ እሱ ግን ኢትዯጵያን ሊያበራ ነው የሞተው” ሲል ሳግ እየተናነቀው ምሬቱን ገልጿል።

ከሐዘንተኞቹ መሐል በቅርብ ቀናት ሟችን በስልክም ይሁን በአካል አግኝተዋቸው ያውቁ እንደሆነ ተጠይቀው ኢንጂነሩ ሥራ ላይ ስለሚያተኩሩ እምብዛም ከቤተሰብ ጋር እንደማይገናኙ የሚያመላክት አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።

“እሱ አገሬን ሥራዬን እያለ ሁሉም ሰው ረስቶታል። እሱ ሁሉ ነገሩ ሥራው ላይ ነው። ዘመድ አይልም…” ስትል ስሟን መግለጽ ያልፈለገች የቤተሰብ አባል። “ከሰው ጋር አልኖረም፤ በረሃ ነው የኖረው” ስትል ሟች ማኅበራዊ ሕይወት የሚባል ነገር እንኳ እንዳልነበራቸው ተናግራለች።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.