NEWS: Sanctions and Politics | የ”ጥርስ አልባው” ማዕቀብ መነሳት ፖለቲካ?

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝታቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ እንዲነሳ ከጥቂት ቀናት በፊት አዲስ አበባ ለተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉትሬዝ ይፋዊ ጥያቄ አቅርባለች።

ሰላምና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ተፋጠው የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ተቃዋሚዎቻቸውን ከመደገፍ በተጨማሪ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣልባት በከፍተኛ ሁኔታ ግፊት ማድረግ ጀመረች።

በአፍሪካ ህብረት በኩል ቀጥተኛ ጥያቄና በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በኩል ደግሞ በተዘዋዋሪ ግፊት ማድረጓንም ተንታኞች ይናገራሉ።

ወሳኝ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች በ100 ቀናት

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት

ከጦርነቱ በኋላ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚል አቋም ያራምዱ ነበር የሚሉት የግጭት አፈታት ባለሙያ የሆኑት አቶ ኤልያስ ኃብተ-ስላሴ የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ ስልጣን የነበረው የሶማሊያ ፌደራላዊ የሽግግር መንግስት ግብዣ ተከትሎ ወደ አካባቢው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያካሄደ ሲሆን፤ ሁለቱም ባላንጣዎች በሶማልያ ተቃራኒው ቡድኖችን ሲደግፉ ነበር።

የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግስታት በአካባቢው የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት፤ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደ የውክልና ጦርነት ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

“ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ስትሯሯጥ የነበረ ሲሆን፤ ኤርትራም በበኩሏ ኢትዮጵያን የሚጣሉ ኃይሎች እደግፋለሁ” የሚል አመለካከት ነበራት ይላሉ።

ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አሜሪካን የመሳሰሉ አገራት ኤርትራ እስላማዊ አክራሪነትና አሸባሪነትን ትደግፋለች የሚል ምክንያት አቅርበዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት አልሸባብን እንደሚደግፍ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፣ ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ ማራዘሙ ይታወሳል፡፡

በእርግጥም ኤርትራ አልሻባብን በገንዘብና በትጥቅ ትደግፋለች የሚለውን ክስ ኢትዮጵያ በበላይነት የምትቆጣጠረው ኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት በቀጥታ ያቀረቡት ጥያቄ ተከትሎ የሆነ ነበር።

ኤርትራ የሚቀርብባት ውንጀላ ያልተቀበለች ሲሆን የተጣለባትን ማእቀብም መሰረት አልባ ስትል ኣጣጥላው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እርምጃዎች የት ድረስ?

ኤርትራና ኢጋድ

ሁለቱም አገሮች በድንበር ሳቢያ ወደ ጦርነት ማምራታቸውን ተከትሎ እንደ አገናኝ ድልድይ መድረክ ሆኖ ያገለግል እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ሶማሊያ ላይ የተከሰተው ፖለቲካ ቀውስ ሁለቱም በውክልና ለተለያዩ ቡድኖች መደገፋቸውን ተከትሎ በድርጅቱ ውስጥ አለመግባባት መፈጠሩ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በዚህም ምክንያት ድርጅቱ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የሰጠው ውሳኔ ጋር ተያይዞ ኤርትራ በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ ከድርጅቱ ራሷን ማግለሏ ይታወሳል።

ራሷን ከኢጋድ ካገለለች ግዜ ጀምሮ ከአካባቢው አገራትና ከዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ ጋር የነበራት ግንኙነት እየተቋረጠና እየተነጠለች የመጣች መሆኑንን፤ በተለይም ማእቀቡ ኤርትራን ከሌላው አለም እንድትነጠል አድርጓታል ቢሉም ተፅእኖው ከፍተኛ እንዳልሆነ አቶ ኤልያስ ይናገራሉ።

የማዕቀቡ ፋይዳ

“ማዕቀቡ የተገደበ ነበር፤ ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን የጦር መሳሪያ ለኤርትራ ዝውውርን መገደብ፣ ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣናት እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ” የሚያትት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኤልያስ የኤርትራ ህዝብና ኢኮኖሚን በጭራሽ የሚነካ እንዳልነበር ይናገራሉ።

በለንደን ተቀማጭነታቸው ያደረጉት የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱልራህማን ሰይድ በበኩላቸው ማእቀቡ ተግባራዊ ሆኖ አልቆየም ይላሉ።

“የጦር መሳሪያም ዝውውር ይሁን የባለስልጣናቱ ከአንድ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወርና ክፍት ሆኖ ነው የቆየው፤ ማዕቀቡ ድሮም ጥርስ አልባ ነበር” ይላሉ።

ከዚያም በተጨማሪ የተባበሩት ኤምሬትስ ኤርትራ ላይ የጦር ሰፈር መስርታ የመንን ስትመታም ነበር ይላሉ።

“ማዕቀቡ ከተነሳ ለኤርትራ መንግሥት ስርዓት የሞራል ብርታት ይሰጠው ይሆናል” ይላሉ።

ተፅእኖውም እዚህግባ የማይባል በመሆኑም የተለያዩ ሀገራት ማዕቀቡን ለማስነሳት ጅማሮ ላይ የነበሩ መሆናቸውንም አቶ ኤልያስ ይናገራሉ።

ወሳኝ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች በ100 ቀናት

ማዕቀቡ ይነሳ ይሆን?

የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መሻሻል ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ማእቀቡ እንዲነሳ የጠየቀች ሲሆን፤ ኢትዮጵያስ ይህንን ማድረግ ትችላለች ወይ ለሚለው ጥያቄም፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት አባል ስለሆነች ጥያቄውን ማቅረብ የምትችል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኤልያስ የመጨረሻው ውሳኔ የፀጥታ ኃይሉ ነው ይላሉ።

የኤርትራ ወዳጆች የሆኑ ሀገራት የማዕቀቡን እርባና ቢስነትና ውጤታማ አለመሆኑን ጠቅሰው ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ አካላት እንደነበሩም ይናገራሉ።

“በየትም አለም ቢሆን እገዳ አይሰራም፤ በእጅ አዙር እየሰራ ነው” የሚሉት አቶ ኤልያስ በአፓርታይድ ስርዓት ወቅት ማዕቀብ ተጥሎባት የነበረችው ደቡብ አፍሪካ እንዴት ከእስራኤል የጦር መሳሪያ በእጅ አዙር ታገኝ እንደነበር በምሳሌነት ያነሳሉ።

አሜሪካ የተለየ ፍላጎት አላት የሚሉት አቶ ኤልያስ የኤርትራ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና የሶማሊያን ኢስላማዊ ቡድን ለመምታት የአሰብ ወደብን በመስጠት መተባበሯ በምዕራባውያን ዘንድ እንደበጎ አስተዋፅኦ ሊታይ እንደሚችልም ይጠቅሳሉ።

“ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለምዕራቡ አለም ያደረጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፤ ለህዝቡ አልጠቀመመም እንጂ፤ ከነበረው አስተሳሰብ ተቀይሯል” ይላሉ።

ያለውን ለውጥ በማየት አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ፈቃድ ከተጨመረበት በቀላሉ ማዕቀቡ እንደሚነሳ የሚናገሩት አቶ ኤልያስ የቀድሞ አምባሳደርና በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ዶናልድ ያምማቶ ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር መወያየት አንድ ጠቋሚ ነገር ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል አልሸባብን ለመደገፍ የኤርትራ መንግሥት አቅም የለውም የሚሉት አቶ አብዱልራህማን “ኢትዮጵያ ማዕቀቡ ይነሳ ማለቷ በአፍሪካም ሆነ በቀጠናው ካላት ትልቅ ቦታ እንዲሁም በአለም ዓቀፍ ዲፕሎማሲ ተሰሚ መሆኗ ከፍተኛ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል፤ በፍጥነትም ይነሳል” ይላሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.