Natural Ways To Stop Anxiety | ጭንቀትን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለማስወገድ

አሁን ላይ ጭንቀት የበርካቶች የዕለት ተዕለት ችግር እየሆነ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታል።

ከበዛ የስራ ጫና፣ በኑሮ ደስተኛ አለመሆን እና ተያያዥ ምክንያቶች እንዲሁም በማህበራዊ ህይዎት የሚከሰቱ አጋጣሚዎችና በርካታ ምክንያቶች ደግሞ ለዚህ እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ።

የጤና እና የስነ ልቦና ባለሙያዎችም ቀለል ባለ መንገድ ከጭንቀት መገላገል የሚችሉበትን መንገድ ይጠቅሳሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ በጭንቀት ጊዜ አድሬናሊን ሰውነት ውስጥ ስለሚበዛ ይህን ለመቀነስና ለማመጣጠን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ።

እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለጭንቀት የሚዳርጉ ሆርሞኖችን ማስወገድ፣ ከብቸኝነትና ፍርሃት የሚመነጭ ጭንቀትን ለማስወገድና ነጻ ስሜት ለመላበስም ይረዳሉ።

ተመስጦ፦ ተመስጦ በማድረግ ለጭንቀት ከሚዳርጉ ስሜቶችና ሃሳቦች መራቅ ይቻላል፤ ይህን ሲያደርጉ ወደ ውስጥዎ እንዲመለከቱ በማድረግ የበለጠ መረጋጋትን ለማግኘት ይረዳዎታል።

ዘና የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር፦ አንዳንድ ሰዎች በጭንቀት ጊዜ ከውስጣቸው የሚመጣን ስሜት ለማስታገስ በሚል ጥርሳቸውን ሲያፋጩ ይስተዋላል።

ከዚህ አንጻርም ዘና የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን መስራት፤ በጀርባዎ ቀጥ ብለው መተኛትና ከእግር ጣትዎ ጀምረው እስከ ትክሻዎ ድረስ ጡንቻዎን እየወጠሩ ለቀቅ በማድረግ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በየእለቱ መስራት።

ስሜትዎን መጻፍ፦ የሚሰማዎን ነገር መጻፍ በዚህ ወቅት ተመራጩ መንገድ ነው፤ ውስጥዎ ያለውን ነገር መጻፍና ከዚያ በኋላ እረፍት ማድረግ።

ጫና አለማብዛት፦ ከቤተሰብ ጋር የሚያሳልፉትን የመዝናኛ ሰዓት ጨምሮ ለሁሉም ስራዎ የተወሰነ ጊዜ በመመደብ ሁሉንም በልክ እና በአግባብ መከወን።

አደርገዋለሁ ላሉት ነገር ጊዜ መድበው መንቀሳቀስዎ ራስዎ ላይ የሚፈጥሩትን ጫና በመቀነስ፥ በበዛ ውጥረት ሳቢያ ለጭንቀት እንዳይዳረጉም ያግዝዎታል።

ከዚህ ባለፈም ዘና እና ቀለል ባለ መንገድ ስራዎን ሰርተው ውጤታማ ተግባር ያከናውኑ ዘንድም ይረዳዎታል።

 

Advertisement

የሚያዝናናዎትን ነገር ማድረግ፦ ምናልባት ከቤተሰብ ጋር ወጣ ብሎ መዝናናት አልያም ከጓደኞችዎ ጋር መጫወትና ማውራት ብቻ የትኛውም ቢሆን ለእርስዎ የደስታ ምንጭ የሆነውን ነገር በማድረግ ከዚህ ስሜት ለመራቅ ይሞክሩ።

የእኔ ከሚሉት ሰው ጋር መወያየት፦ ሲጨነቁ አዕምሮ ለውጥረት ይዳረጋል በዚህ ጊዜም ምንም ነገር አስበውና በትክክል ለመከወንም አዳጋች ይሆንብዎታል።

በዚህ ጊዜም የእኔ ከሚሉት ይበልጥ ከሚቀርቡትና ከሚያምኑት ሰው ጋር በየትኛውም መንገድ ቢሆን መወያየት መልካም እና ተመራጭ ነው።

ሲወያዩም ታዲያ የሚሰማዎትን፣ ለጭንቀትዎ መንስኤ የሆነውን ጉዳይ እንዲሁም ከዚህ ስሜት ለመውጣት ምን ማድረግ እንደሚገባና መሰል ጉዳዮች ላይ ቀለል ያለ ውይይት ማድረግ።

ምናባልባት ያስጨነቀዎትን ነገር መናገር ካልደፈሩ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየቱም መልካም ነው።

ይህን ሲያደርጉም ቢያንስ ከብቸኝነት እየወጡ በመሆኑ በጭንቀትዎ ወቅት ይፈሩት የነበረውና አዕምሮ ውስጥ ያለውን መጥፎ ስሜት በማስወገድ፥ ይበልጥ ደህንነት እንዲሰማዎት ስለሚያደርግ በራስ የመተማመን ስሜትዎን ከፍ ያደርገዋል።

ከእንስሳት ጋር ጥቂት ጊዜ ማሳለፍ፦ በዚህ መልኩ ጊዜዎን ማሳለፍዎ ከነበሩበት ስሜት ለመውጣት ያግዝዎታል፤ ይህም ከእንስሳቱ እንቅስቃሴና ከሚያደርጉት ነገር ጋር ተያይዞ ያንን ስሜት የማስወገድ እድል ያገኛሉ።

በተጨማሪም የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ያሉት ሻይን መጠጣት ለዚህ መፍትሄ መሆኑን የስነ ልቦና እና የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከከተማ ወጣ ያለና በተፈጥሮ የተዋበ ቦታን መርጦ በዚያ ማሳለፍም ተመራጭ መሆኑን ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚገልጹት።

ያስጨንቀኛል ባሉት ጉዳይ ላይ ትኩረት አለማድረግ፦ ከምንም በላይ ጭንቀት በሂደት የሚመጣና ችግሩም እየተንሰራፋ የሚሄድ እና ያሉበትን ዓለም በማስጠላት ለህይዎት ጥሩ ግምት እንዳይኖር የሚያደርግ ችግር ነው።

በመሆኑም የጭንቀት ስሜት ሲሰማዎት መልካም ነገሮችን ማሰብና በዚያ ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ስለ ሚያስጨንቅዎት ጉዳይ አለማሰብ መርሳትና የተሻለውን ለማድረግ መሞከርም ትልቁ መፍትሄ ነው።

Advertisement

4 Comments

Comments are closed.