BBC: Activist Jawar Mohammed To Return To Ethiopia | አክቲቪስት ጃዋር ሞሐመድ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስና ለውጡን ለመደገፍ እንዳሰበ ተናገረ.

ጃዋር መሀመድ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት በኦሮሚያ የተካሄዱ አመጾችን ከጀርባም ከፊትም ሆኖ በማስተባበር ይታወቃል። የሚወዱትም ሆነ የሚጠሉት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስል ውስጥ ሊፍቁት አይቻላቸውም።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ለታየው ፖለቲካዊ ለውጥ የእርሱን የትግል ስልት በዋነኝነት የሚያነሱም በርካታ ናቸው። ናይሮቢ ለስራ በመጣበት ወቅት ሶስት ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሰንዝረንለታል።

ቢቢሲ አማርኛ- በዚህ ወቅት ሀገር ቤት ለመግባት ምክንያትህ ምንድን ነው?

ጃዋር፤- መጀመሪያም እኤአ በ2003 በ 17 አመቴ ከሀገር የወጣሁት ለትምህርት ነው። ከዛ በኋላም እየተመላለስኩ በየዓመቱ ጥናቴን የምሰራው እዛው ነበር። ነገሮች ከመንግስት ጋር እየተካረሩ ሲመጡ እንዲሁም ደግሞ ውጭ ቆይቼ ትግሉን መርዳት የምችልበት መንገድ ስለተገኘ ባለፉት ዓመታት ትግሉን በማህበራዊ ሚዲያም፣ በሚዲያም፣ በአካዳሚውም ትግሉን ስረዳ ነበረ። ያ ትግል ባይቋጭም በአብዛኛው ውጤት አምጥቷል። የነደፍነው ስልት ውጤት አምጥቶ በስርዓት ውስጥ ለውጥ አምጥቷል። የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ ነው ያለው። ወደ ዲሞክራሲ የምናደርገው ሽግግር በፍጥነት እየተካሄደ ነው ። ከዚህ አንፃር ውጭ ከመቆየት ሀገር ውስጥ ገብቶ መስራት ይረዳል። በተለይ ደግሞ እየተደረገ ላለው ሽግግር ምሁራዊ እርዳታ፣ በሚዲያውም ፣ ህዝብን በማስተባበር እርዳታ ማድረግ ያስፈልጋል። ገዢው ፓርቲ ላይም ጫና በመፍጠር ሽግግሩ በፍጥነት እንዲሄድና የተቃውሞ ኃይሉም በፍጥነት እየተዘጋጀ ለሽግግሩ አቅሙ እየጎለበተ እንዲሄድ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ በትምህርትም በልምድም ያለኝን ለማካፈል ሚዲያውንም ደግሞ ለመምራትና ለማጠናከር አስፈላጊ ነው ብዬ ስላመንኩ በዚህ ወቅት ለመሄድ ወስኛለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ፤- አንተ የምትታወቅበት የትግል ስልት አለ። ከዚህ በኋላ ያ የትግል ስልት ነው የሚቀጥለው ወይስ ሌላ የትግል መንገድ ይኖርሃል?

ጃዋር- የምትለው የሰላማዊ ትግሉን መሰለኝ። ሰላማዊ ትግል በተለያየ መልኩ ልትጠቀመው ትችላለህ። አንደኛው አምባገነናዊ ስርአትን ለመጣል ልትጠቀመው ትችላለህ። ከጦር የተሻለ ውጤት አለው። በዚህ የዛሬ አስራ ምናምን ዓመት ስከራከር ሰዎች ይስቁ ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጣው ለውጥ ትልቅ መስዋዕትነት ተከፍሏል፤ ግን በጦር ቢሆን ኖሮ መስዋዕትነቱ እጥፍ ድርብ ነበር። የሚመጣውም ለውጥ ከፍተኛ ውድመትን ሊያስከትል ይችል የነበረ ሲሆን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገርም ብዙ እድል አይኖርም ነበር። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል በህዝባችን ውስጥ እንዲተዋወቅና ህዝባችን ከውጭ ያሉ ወይም ደግሞ በጫካ ያሉ አማፅያንን ከመጠበቅ ይልቅ በየቦታው በየሰፈሩ እንዲታገል ማድረጉ ጠቃሚ ነው። እና ሰላማዊ ትግል አምባገነን ስርዓትን ለመጣል ይረዳል። በሁለተኛነት ደግሞ አምባገነናዊ ስርዓትን ከገለበጥክ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ይረዳል። አሁን እያየህ ያለኸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደረገው ድጋፍ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን ለውጥን ለማበረታታትና ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲፋጠን ሽግግሩን የሚያደናቅፉ ኃይሎችን ተስፋ ለማስቆረጥም ነው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል አምባገነናዊ ስርዓትን ለመገልበጥም ከዛ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባትም ይረዳሃል ማለት ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኃይል ሁለት ነው። አንድ የመንግስት ኃይል ሁለተኛው የህዝብ ኃይል አለ። የመንግስት ኃይል አሁንም ባብዛኛው ለውጥ በማይፈልጉት እጅ ነው ያለው። እነሱ ናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠልፈው ሊጥሉ የነበሩት። ግን ህዝባችን በሰላማዊ ትግል በደንብ ስለታነፀ በቀላሉ ሊያከሽፍባቸው ቻለ።

ወደ ዲሞክራሲ ከተሸጋገርን በኋላም ይህ ስልት ይረዳል። ፀረ ሙስና ላይ መስራት ትችላለህ። የሚዲያ ኃላፊነትን የማጠናከር ስራ ላይ ማተኮር ትችላለህ። በህዝቦች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የምትከላከልበት ብዙ ስልቶች አሉ። እነዚህን ነገሮች ማስተማር እፈልጋለሁ። ሀገር ቤት ስገባ አንዱ ማድረግ የምፈልገው ከሚዲያው አንፃር ‘ቲንክ ታንክ’ ማቋቋም እፈልጋለሁ ። ከዛው ጋር በተያያዘ ደግሞ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአመራር ስልጠና ተቋም በተለይም ከስር የሚወጣውን ወጣት ብቁ አመራር እንዲወጣው ለማድረግ። ሀገራችን ብዙ ስጦታ አላት፤ ብዙ ልጆች ይወለዳሉ፤ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የአመራር ክህሎትን በተፈጥሮ እንዲሁም በትምህርት ታገኘዋለህ። የተፈጥሮ ክህሎት ያላቸውን ልጆች በማሰልጠንና በማጠንከር እንዲተዋወቁ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ማድረግ ይቻላል፤ እዚህ ላይ እንግዲህ እኔም የተማርኩት አለ ከኔም ጋር የሚሰሩ ባልደረቦች አሉ፤ በዚህ ላይ መስራት እንፈልጋለን ወደፊት።

ቢቢሲ አማርኛ፤- ብዙ ጊዜ ለነፃነትና ለለውጥ ሲታገሉ የሚቆዩ ሰዎች እድሉን ካገኙ በኋላ ጭልጥ ካለ ተቃዋሚነት ወደ ጭልጥ ያለ አመስጋኝነት የሚዘዋወሩበት አጋጣሚ ይኖራል። አንተን የምናውቅህ ስርአቱን በመንቀፍ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች ጋር ያለህ መልካም ግንኙነት ወትሮ የምትታወቅበትን የትግል መልክ ምን ያህል ይለውጠዋል?

እኔ እንደውም የምፈራው ቋሚ ተቃዋሚ እንዳልሆን ነው። ምክንያቱም እኔ አንደኛ የመንግስት ስልጣን የመያዝ ፍላጎት የለኝም። መንግስት ሲባል ደግሞ ሁሌም መግፋት አለብህ። የኛ ወጣቶች ማወቅ ያለባቸው መንግስት ሁሌም ካልገፋኸው አስቸጋሪ ነው።መደገፍ ጥሩ ነው። ግን ከደገፍከው ውስጥ ገብተህ ባለህ እውቀትና ባለህ ችሎታ መርዳት መቻል አለብህ። ከኦህዴድ ልጆች ጋር ስንከራከር የነበረውም ይህው ነው።ኦህዴድን የሚደግፉ ልጆች ቁጭ ብሎ ለኦህዴድ ማጨብጨብ ዋጋ የለውም። ለአብይ ሰልፍ መውጣት ማጨብጨብ የአንድ ቀን ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በመለስ ዜናዊ እና በኢህአዴግ ጊዜ እውቀት ያለው ችሎታ ያለው ተገፍቶ ወጥቷል። አሁን ያን ችሎታና እውቀት ወደ ሀገር በመመለስ የሀገሪቷን ቢሮክራሲ ውስጥ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች አቅምን መጨመር ያስፈልጋል።

መንግስትን የሚወዱ፣ አብይን የሚወዱ የተለወጠውን ኢህአዴግን እንወዳለን የሚሉ ሰዎች ማጨብጨብ አይደለም የሚያስፈልጋቸው። ገብተው በችሎታቸው መርዳት መቻል አለባቸው። ብዙዎች ደግሞ እየገቡ እየረዱ ነው።በፖለቲካ መንግስት ውስጥ መግባት የማንፈልግ ነገር ግን በሲቪክ ማህበረሰቡ ውስጥ መቆየት የምንፈልግ ሰዎች ወደድንም ጠላንም ተቃዋሚ ሆነን ነው የምንቀጥለው። ተቃዋሚ እንደተቃዋሚ ፓርቲ ሳይሆን የመንግስት ተቺዎች ሆነን ነው የምንቀጥለው። ምክንያቱም አክቲቪስት ከሆንክ ልትረካ አትችልም። ምንም ቢያደርግ መንግስት ሊያስድስትህ አይችልም። ምክንያቱም አንድ ነገር ከሟላልህ አሁንም ሌላ የሚጎድል ነገር አለ። አይደለም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፍትህ እጦት ፣ የኢኮኖሚ ችግርና ብዙ ነገሮች ያሉበትን ሀገር ተውና እኔ በምኖርበት አሜሪካ ወይንም ደግሞ ገነት በምትላት እንደ ስዊድንና ኖርዌይ ራሱ አክቲቪዝም መሰረታዊ ፍላጎት ነው።

ሙስናን ለመታገል መንግስት ብቃቱ እንዲጨምር አቃቂር እያወጣህ መግፋት መቻል አለብህ። እናም ወደፊት በማደርገው ሂደት እርግጥ ነው ከዚህ በፊት እንደማደርገው ጭልጥ ያለ ተቃውሞ ውስጥ መቀጠል አልችልም። ይሄንን አፍርሱ ይሄንን ናዱ ማለት አልችልም። ምክንያቱም እኔና ሌሎች ያለብን አንዱ ችግር ባለፉት አራት ዓመታት ወጣቱ መንግስት እንዲያፈርስ (ወጣቱ መንግስት የማፍረስና የማሽመድመድ) አሰልጥንነዋል። በአሁኑ ወቅት እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር መንግስት አለ ማለት አይቻልም። ከታች ያለውን መዋቅር አሽመድምደነዋል።ይህን ወጣት እንደገና ዲሞክራሲን የመገንባት ፤ ሀገርን መልሶ የመገንባት ክህሎት ማስተማር መቻል አለብን። እና ያንን ከመንግስት ጋር እየተረዳዳን የምንሰራው ብዙ ነገር አለ።

በተለይ ደግሞ አሁን ባለው ሽግግር ላይ መንግስትን ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እደግፋለሁ። ምክንያቱም ሀገሪቱ ወደ ገደል እየሄደች ሳለች ነው ትንሽ ያስቀየሳት እርሱ። ወደ ገደል ሊመሯት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር መሆን አንችልም። አሁን ያለን እድል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመቆም የሚያጠፋቸውን ነገሮች እየተቸን ግን በተለይ ይህንን ለውጥ ሊያኮላሹና ሊያከሽፉ የሚፈልጉ ኃይሎች ባለን ተሰሚነትና ባለን እውቀት ባለን ስልት እያዳከምን ሀገሪቷን ወደፊት ማሻገር አለብን።

ሀገሪቷ ወደ ብጥብጥ እንዳትሄድ እንደገና ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም አምባገነን ሊያደርጉት ይችላሉ። እየነካኩ ከሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይል ወደ መጠቀም ወደ አምባገነንነት የሚሄድበት እድል ሊኖር ይችላል። ፈልገው ሳይሆን ሳያውቁ አምባገነን የሆኑ ብዙ አምባገነኖች አሉ። ሁኔታዎች ወደዛ ይገፏቸዋል።

አለበለዚያ ደግሞ እርሱን ገልብጠው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያስገቡን ለምሳሌ አሁን በድጋፍ ሰልፉ ላይ ቢገሉት ኖሮ ለውጥን የሚደግፈው የኛ ወገንም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድበት ሁኔታ ነበረ። ያ ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይከተናል። እና እዛ ውስጥ እንዳንገባ ከመንግስት ሰዎች ጋር እንወያያለን።

በበለጠ ደግሞ የተቃውሞውን አቅም ማጠናከር እፈልጋለሁ። እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም ። ግን ክህሎቶች አሉኝ የተማርኳቸው ስልቶች አሉ ። እድሜ ልኬን ይሄንን ነው የሰራሁት። በዚህ የተቃውሞ ኃይል ወደ አንድ እንዲመጣ እንዲጠናከር የሚሰራውን ስራ በስትራቴጂ እየደገፈ እንዲሄድ እፈልጋለው። ጠንካራ ተቃዋሚ የሌለበት ሀገር ውስጥ ዲሞክራሲን መገንባት አትችልም፤ የአማራጭ ፖሊሲዎች ብፌም ሊኖረው ይገባል የኛ ህዝብ። ዝም ብሎ ዶሮ ወጥ ቢበላ የኛ ህዝብ ይደብረዋል ሽሮ መኖር አለበት። እና ይሄ የተወዳዳሪ እድል ምርጫ ሊኖረው ይገባል የኛ ህዝብ።

እኛና ሌሎች ባለፉት ዓመታት ስርዓቱን የማዳከም ስራ ስርተናል። በጣም በተዋጣ መልኩ። በ2020 እዚህ እንደርሳለን እንል ነበር። ነገር ግን ፍጥነቱ በጣም ስለሄደ አሁን እዚህ ደርሰናል። እርሱ ራሱ ችግር አለው። አሁን ደግሞ በተቀሩት አመታት አትሊስት በ2020 ወደ ሙሉ ዲሞክራሲ እንድንሸጋገር ከዛ በኋላ ደግሞ የተሸጋገርንበት ዲሞክራሲ እየተጠናከረ እንዲሄድ የሚመጣው መንግስት በተለይ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን እየፈታ እንዲሄድ እናስባለን። አሁን እዚህ የመጣሁት (ናይሮቢ) አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩት ያሉት ሁኔታ አለ። ለምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደት በጣም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ እምቅ ኃይል አላት ትልቅ የሆነ ሃብትም አላት። ይህንን ሃብት ከአካባቢው ህዝቦች ጋር የኢኮኖሚ ቁርኝት በማድረግ ማሳደግ መቻል አለባት። ከኤርትራ ጋር እየተደረገ ያለው ነገር በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ሰዎች ከኤርትራ ጋር ያለውን ጉዳይ ከፖለቲካ አንፃር ብቻ ነው እያዩ ያሉት። ፖለቲካውን ለጊዜው ገሸሽ አድርገነው ኢኮኖሚው ላይ እያተኮርን መሄድ መቻል አለብን። ከሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ መሄድ መቻል አለበት። ከኬኒያ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ መሄድ መቻል አለበት።

ይሄንን መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ይሰራል። እኛ ደግሞ ያንን መንግስት የሚያመጣውን ፖሊሲ አስቀድመን ጥናት በማድረግ በተለያዩ ኮንፍረንሶች በተለያዩ የጥናት ወረቀቶች በተለያዩ ሚዲያዎች ህዝቡን ማዘጋጀት መቻል አለብን። እና እንግዲህ እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ ነው መስራት የምፈልገው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.