NEWS: ትራምፕ፡ “ስደተኞችን በፍጥነት ጠራርጎ ማባረር ያስፈልጋል”

ዶናልድ ትራምፕ ሕገወጥ ስደተኞችን ወለም ዘለም ማለት ሳያስፈልግ ጠራርጎ በፍጥነት ከአገር ማባረር እንደሚፈልጉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው እያነጋገረ ነው።

ትናንት ዕሑድ በግል የትዊተር ገጻቸው እንዳሉት “አንድ ስደተኛ አሜሪካ ሲረግጥ ፍርድቤት፣ ዳኛ ገለመሌ ሳይባል ወደመጣበት መሸኘት ያሻል” ብለዋል።

ይህን ያሉት ውግዘት ካስተከተለባቸውና የስደተኞች ልጆችን ከወላጆቻቸው የሚለያየውን ፖሊሲ ለመቀልበስ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ ነው።

በዚህ ራሳቸው ትራምፕ መልሰው በቀለበሱት ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ ከ2ሺ በላይ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር እንዲለያዩ ምክንያት ሆነው ነበር።

“ይሄ ሁሉ ስደተኛ አገራችንን መውረር ሊፈቀድለት አይገባም። ወዲህ ወዲያ ሳይባል ወደመጣበት መመለስ ነው የሚያሻው” ብለዋል ትራምፕ።

ጨምረውም “ስደተኛ መቀበል ካለብንም በችሎታና አቅም እንጂ…” ሲሉ በኢኮኖሚ ስደተኞች ላይ ያላቸውን የማይናወጥ አቋም ገልጸዋል።

ትራምፕ በሰኔ 20 ልጆችን ከወላጆች የሚለያየውን የስደተኞች ፖሊሲን መልሰው ለመቀልበስ የተገደዱት ውሳኔያቸው ዓለማቀፍ ውግዘት ካስከተለባቸው በኋላ ነበር። እርሳቸውም ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም ይህንኑ ፖሊሲ መልሰው ሽረውታል።

“ኋላ ላይ ሳስበው…ቤተሰብን መለያየቱ ጥሩ ስሜት አልሰጠኝም” ብለው ነበር፣ ውሳኔያቸውን በቀለበሱበት ወቅት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ውሳኔውን የቀለበሱት ባለቤታቸው ሜሊና እና ሴት ልጃቸው ኢቫንካ ውሳኔውን እንዲቀለብሱ ስለወተወቷቸው እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ትራምፕ የአሜሪካ ስደተኛን የመቀበል ፖሊሲ በሌላው ዓለም መሳቂያ መሳለቂያ እንደሆነ ደጋግመው ይናገራሉ። በተለይም በሕገወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ስደተኞችን ያለምንም ርሕራሄ ወደመጡበት ጠራርጎ ማባረር እንደሚያስፈልግ አጽእኖት ሰጥተው ይከራከራሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.