NEWS: ”መስቀል አደባባይ በነበረው ታሪካዊው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ቦንብ በቦርሳቸው የያዙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል”

ኢቲቪ እያስተላለፈ በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፍ ቀጥታ ስርጭቱ ላይ እንደታየው ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ቀጥሎም መድረኩ አካባቢ የነበሩ ግለሰቦች ሲሯሯጡ ተስተውሏል።

ዛሬ በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተከሰተውን ጥቃት በማስመልከት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በቀጥታ በተላለፈው በዚህ መግለጫቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ”ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተደምረው ፍቅር እንዲዘንብ ያደረጉበት ዕለት ቢሆንም የአገራችንን ሰላም የማይፈልጉ አካላት በተጠና እና በታቀደ መልኩ ሙያቸውን ታግዘው ይህን ደማቅ ስነ-ስርዓት ለማደፍረስ የሰው ህይወት ለመቅጠፍ እና ደም ለማፍሰስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።

አጠቃላይ አላማቸው የከሰረ እና የወደቀ ቢሆንም ጥቂት ኢትዮጵያውያን እንዲጎዱ ሆነዋል ሲሉም ተናግረዋል። ህይወታቸው ያለፈ እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቼ ቤተሰብ ሁሉ መጽናናት እመኛለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ መሰዋትነት ለኢትዮጵያውያዊነት የተከፈለ መሰዋትነት እንደሆነ እና ሁሌም የምናስታውሰው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጥቃት አድራሾቹ ”ትናንት አልተሳካላችሁም፤ ዛሬም አልተሳካላችሁም ነገም አይሳካላችሁም። ፍቅር ያሽንፋል። መግደል መሸነፍ ነው።” የሚል መልዕክትን አስተላልፈዋል።

የድጋፍ ሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉደታ ገላልቻ በበኩላቸው ይህ ጥቃት ያደረሱት እየተካሄደ ያለው ለውጥ ወደፊት እንዳይሄድ የሚሹ ቡድኖች ናቸው ብለዋል።

”እሰካሁን ባለኝ መረጃ አንድ ሰው ህይወቱን አጥቷል አንድ ሌላ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሷል” የሚሉት አቶ ጉደታ ከዚህ በተጨማሪ ቦንብ በቦርሳ ይዘው የነበሩ ግለሰቦች በህዝብ ቁጥጥር ስር ውለው ለፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል ብለዋል።

”ደህንነትን በተመለከት ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመሆን በቅንጅት ስንሰራ ነበር አሁን የተፈጠረው ግን ከደህንነት አካላት በኩል ክፍተት መኖሩን አሳይቶናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህ ይሁን እንጂ ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት አስተላልፈናል የድጋፍ ሰልፉም አላማ ተሳክቷል ብለዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን በቦታው የነበረው ባልደረባችን አምቡላንሶች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ይዘው ወደ ሆስፒታል ይዘው ሲገቡ ተመልክቷል።

አርባ ያህል ሰዎች በቦምቡ ጥቃትና በመረጋገጥ ምክንያት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመጡ ሲሆን ሰላሳዎቹ የአጥንት መሰባበር፤ አስሩ ያህሉ ቅንጭላታቸው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።

ጉዳቱ የከፋ በመሆኑም ለሪፈራል ወደ ሚኒልክና አቤት ሆስፒታል እንደተላኩ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ነርስ ለቢቢሲ ገልፀፃለች።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልፀዋል።

15 በሚደርሱት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በተቀሩት ላይ አነስተኛ እና መካከለኛ ጉዳት እንደደረሰም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከፍንዳታው በኋላ ሰዎች ሲሯሯጡ እና ሲገፋፉ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልፀዋል።

” የጸጥታ ሃይሎች ብዙ ተግባር አከናውነናል ይሁን እንጂ ጥቃት አድራሾቹ ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው ስለነበር ጥቃቱ ሊፈፀም ችሏል” ብለዋል።

ምርመራዎችን እያካሄዱ እንደሆኑ ጠቅሰው ውጤቱም ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ ዛሬ በመስቀል አደባባይ የተሰነዘረውን ጥቃት አውግዘዋል።

አምባሳደር እስጢፋኖስ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ”ሁከትን ለማነሳሳት የተደረገውን ሙከራ ኤርትራ አጥብቃ ታወግዛለች”

ጨምረውም በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲህ አይነት ጥቃት ሲሰነዘር በታሪክ የመጀመሪያ ነው ብለዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.