“ትናንት አልተሳካላችሁም፤ ዛሬም አልተሳካላችሁም ነገም አይሳካላችሁም ፤ ፍቅር ያሽንፋል” ዶ/ር አብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሀገሪቱ ላይ እያከናወኗቸው ላሉ በጎ አስተዋፅኦዎች ድጋፍ ለማድረግ መስቀል አደባባይ ሰልፍ እየተካሄደ ባለበት ወቅት የቦምብ ጥቃት ደርሷል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ቀጥሎም መድረኩ አካባቢ የነበሩ ግለሰቦች መሯሯጣቸውን የኢቲቪ ቀጥታ ስርጭት ከቦታው አሳይቷል።

ድጋፍ ሰልፉ ላይየተከሰተውንም ጥቃት በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በቀጥታ በተላለፈው በዚህ መግለጫቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ”ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተደምረው ፍቅር እንዲዘንብ ያደረጉበት ዕለት ቢሆንም የአገራችንን ሰላም የማይፈልጉ አካላት በተጠና እና በታቀደ መልኩ ሙያቸውን ታግዘው ይህን ደማቅ ስነ-ስርዓት ለማደፍረስ የሰው ህይወት ለመቅጠፍ እና ደም ለማፍሰስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል” ብለዋል።

የጉዳት አድራሾቹን አላማ ያጣጣሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አጠቃላይ አላማቸው የከሰረ እና የወደቀ ቢሆንም ጥቂት ኢትዮጵያውያን እንዲጎዱ ሆነዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

ህይወታቸው ላለፈው እና ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦች መፅናናትን ተመኝተው” ይህ መስዋዕትነት ለኢትዮጵያውያዊነት የተከፈለ መሰዋትነት እንደሆነ እና ሁሌም የምናስታውሰው ነው” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጥቃት አድራሾቹ ”ትናንት አልተሳካላችሁም፤ ዛሬም አልተሳካላችሁም ነገም አይሳካላችሁም። ፍቅር ያሽንፋል። መግደል መሸነፍ ነው።” የሚል መልዕክትን አስተላልፈዋል።

የድጋፍ ሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉደታ ገላልቻ በበኩላቸው ይህንን ጥቃት ያደረሱት እየተካሄደ ያለው ለውጥ ወደፊት እንዳይሄድ የሚሹ ቡድኖች ናቸው ብለዋል።

”እሰካሁን ባለኝ መረጃ አንድ ሰው ህይወቱን አጥቷል አንድ ሌላ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሷል” የሚሉት አቶ ጉደታ ከዚህ በተጨማሪ ቦንብ በቦርሳ ይዘው የነበሩ ግለሰቦች በህዝብ ቁጥጥር ስር ውለው ለፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል ብለዋል።

አቶ ጉደታ ጨምረውም የድጋፍ ሰልፉን ደህንነት በተጠናከረ መልኩ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በቅንጅት መስራታቸውን አረጋግጠው ከደህንነት አካላት በኩል ክፈተት መኖሩን መገንዘባቸውን ገልፀዋል።

“ይሁን እንጂ ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት አስተላልፈናል የድጋፍ ሰልፉም አላማ ተሳክቷል” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ጥቃቱን አስመልክቶ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ጥላቻን በፍቅር እናሸንፈዋለን። አንዳንድ በጥላቻ ተሞሉ ግለሰቦች የቦምብ ጥቃት አድርሰዋል።”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ነው ያሉት አቶ ፍፁም ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦችንም “የሰላምና የፍቅር ሰማዕታት” ብለዋቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኃዘን መልዕክት አስተላልፈው ጉዳት ያደረሱትም ለፍትህ ይቀርባሉ ብለዋል።

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ ዛሬ በመስቀል አደባባይ የተሰነዘረውን ጥቃት አውግዘዋል።

አምባሳደር እስጢፋኖስ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ”ሁከትን ለማነሳሳት የተደረገውን ሙከራ ኤርትራ አጥብቃ ታወግዛለች”

ጨምረውም በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲህ አይነት ጥቃት ሲሰነዘር በታሪክ የመጀመሪያ ነው ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረትም በፌስቡክ ገፃቸው ከልብ የመነጨ ኃዘን እንደተሰማቸው ገልፀው ለኢትዮጵያ ህዝብም መፅናናትን ተመኝተዋል።

Source: BBC

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.