“Free Andargachew or I Will Resign” | “አንዳርጋቸው ይለቀቅ አለበለዚያ ሥልጣኔን እለቃለሁ”

ማክሰኞ ግንቦት 21 2010 ዓ.ም ከእስር የተፈቱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ነፃ ከወጡ በኋላ በቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ከተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል ባሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተገናኝተው ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ መወያየታቸውን ለቢቢሲ ሃርድ ቶክ ተናግረዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት ለየትኛውም የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሳይናገሩ ቆይተው ለቢቢሲ አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተው ተናግረዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለየያዩ ተፎካካሪ ኃይሎች ጋር ምን አይነት እርምጃ ለመውሰድ ስለማሰባቸው እንደገለፁላቸውና በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እምነት እንዳደረባቸውም ገልፀዋል።

“ሰው እየሳቀ መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ ነበር ያልኳቸው” አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢህአዴግ ውስጥ የእርሳቸውን መፈታት የማይፈልጉ ግለሰቦች እንደነበሩ እንደነገሯቸውና እርሳቸው ግን “ልቀቁት አለበለዚያ ሥልጣኔን እለቃለሁ” በማለት እንደተከራከሩ እንደነገሯቸው ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእርሳቸው መለቀቅ ያላቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት አደጋ ላይ መጣላቸውን መስማታቸው ለመቀራረባቸው አንድ ምክንያት እንደሆነ አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል።

“እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛ ቃላት ናቸው፤ ደግሞም አምናቸዋለሁ፤ ምክንያቱም በግንባሩ ውስጥ የእኔን መፈታት በተመለከተ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተግዳሮት አውቃለሁ” ሲሉ ለቢቢሲ ሃርድ ቶክ ገልፀዋል።

የትጥቅ ትግልና ግንቦት 7

ለአቶ አንዳርጋቸው የትጥቅ ትግል ማድረግ የድርጅታችሁ መሰረታዊ አቋም ነው ተብለው ሲጠየቁ በ1997 ምርጫ ወቅት የተከሰተውን ከተመለከትን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የወሰደው እርምጃ ወደ አንድ ጥግ ገፍቶናል ብለዋል።

ከዚያም በኋላ በየትኛውም የትግል ስልት ለመሳተፍ ወሰንን ሲሉም አስረድተዋል። ይህንን በይፋ ካወጅን በኋላ ግን አንድም ጥይት ኢትዮጵያ ውስጥ ተኩሰን አናውቅም ሲሉም አክለዋል።

እርስዎ በሽብረ ተግባር በመሰማራት ከተከሰሱ እና በሌሉበት ከተፈረደብዎ በኋላ በበላይነት የሚመሩት ግንቦት 7 በተለያየ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ፤ በሰሜን ጎንደር የተለያዩ ጥቃቶችን እንዳደረሰ ሲገልፅ በአርባምንጭ ደግሞ 20 ወታደሮችን እንደገደለና 15 እንዳቆሰለ ገልጿል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም ስለጥቃቶቹ በወቅቱ መግለጫ ሰጥተዋል ተብለው የተጠየቁት አቶ አንዳርጋቸው “በእስር ላይ ብሆንም ግንቦት 7 አንድም ጥይት በኢትዮጵያ ምድር እንዳላጮኸ ነው የማውቀው።”

ብርሃኑም ቢሆን አጠቃላይ ያለውን ተቃውሞ እና እምቢተኝነት መግለፁ ይሆናል በማለት በእስር ላይ እያሉ ምንም አይነት መረጃ ይደርሳቸው እንዳልነበር ጨምረው ገልፀዋል።

አክለውም ከተፈቱም በኋላ እንዲህ አይነት እርምጃ ስለመወሰዳቸው ማንም እንዳልነገራቸው አስረድተው ከግንቦት 7 ይልቅ ሌሎች በሀገሪቱ የታጠቁና የሚታገሉ ኃይሎች ይህንን እርምጃ ወስደዋል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።።

በተጨማሪም አሁን በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ባለበት መልኩ እየተሻሻለ ከሄደ እና እርምጃው ካሳመናቸው የትጥቅ ትግልን ከማውገዝ ወደኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.