Ambasador Taye on PM Abiy’s Visit | አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጉብኝት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሁለት ቀናት በግብጽ ያደረጉትን ቆይታ አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በተለያየ ምክንያት ግብጽ ውስጥ ከነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ አውሮፕላን አዲስ አበባ ገብተዋል።

”ለጉብኝት የዛሬ አምስት ዓመት ወደ ግብጽ የመጣው ኢትዮጵያዊ አንድ ወዳጁ እቃ እንዲያደርስለት ይጠይቀዋል። እንደተባለውም እቃውን ወደ ግብጽ ይወስዳል። ይዞት ወደ ግብጽ የመጣው እቃ (ጫት) ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው እንደልቡ የሚጠቀመው ነገር ቢሆንም ግብጽ ውስጥ ግን ክልክል ነው ተብሎ በፍተሻ ወቅት በቁጥጥር ሥር ይውላል።”

የዚህ ኢትዮጵያዊ ታሪክ እጅጉን አሳዝኖኛል ያሉት በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ እስከሚፈታባት ቀን ድረስ ለአምስት ዓመታት በእስር ላይ እንደነበር ገልጸዋል።

”ይህ ሰው ሥራውን አጥቷል፤ ሕይወቱ ተመሰቃቅሏል። በዚህ ሁሉ ዓመት የእስር ቤት ቆይታው፤ ፍርድ ቤት የቀረበው የዛሬ ሦስት ወር ነበር።” በማለት በእስር ቤት ውስጥ ብዙ እንግልት እና ስቃይ እንደደረሰበት አምባሳደሩ ተናግረዋል።

መፈታቱን እስካሁን ድረስ እንዳላመነ እና ከመፈታቱ ባለፈ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በአንድ አውሮፕላን ወደ ሃገሩ መመለስ በመቻሉ ደግሞ እጅግ መደሰቱን ገልጸዋል።

ከእስር ከተፈቱት ሰዎች በተጨማሪ ኤርትራ ውስጥ የነበሩ እና በቅርብ ወደ ግብጽ የገቡት የቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አባላት ኮሎኔል አበበ ገረሱ እና የኦህዴድ መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ዮናታን ዲቢሳ ወደ ሃራቸው ተመልሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በግብጽና ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ጋር የነበራቸው ውይይት ምን እንደሚመስል አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን ቢቢሲ አነጋግሯቸዋል።

በውይይቱ ወቅት በመሪዎቹ መካከል የነበረው የእርስ በእርስ መግባባት እና መከባበር በጣም አስገርሞኝ ነበር በማለት የጀመሩት አምባሳደር ታዬ፤ ”እስካሁን ባየሁት ነገር የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ብዙ ርቀት እንደሚጓዝ ተሰፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከልም አንዱ፤ ሁለቱን ሃገራት ያስተሳሰረው የአባይ ወንዝ እና ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለው የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ነው።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የግብጽ ሕዝብን ለማስራብ እንደሆነ አብዛኛዎቹ ግብጻውያን ያምናሉ ያሉት አምባሳደሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር እና የግብጽ ሕዝብን በቅርብ ለማግኘት ነበር ብለዋል።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የኢትዮጵያ እድገት የግብጽ ልማት ነው በማለት ኢትዮጵያ ለልማቷ በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የግብጽ ትብብር እንደሚኖር እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማድረግ ዝግጅትም ፍላጎትም እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

እንደ አምባሳደሩ ከሆነ ሌላኛው መሪዎቹ የተወያዩበት ጉዳይ ሁለቱን ሃገራት ሱዳንንም ጨምሮ በመሠረተ ልማት የማገናኘቱ ሂደት ነበር። ”በውይይቱ መሠረት በባቡር መስመር፤ በአስፋልት መንገድ እና በውሃ ትራንስፖርት ሃገራቱን የማስተሳሰሩ ሥራ እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል ተወያይተዋል”።

ከዚህ በፊትም ተቋቁሞ የነበረውን የመሰረተ ልማት ፈንድ የበለጠ ለማጠናከር ደግሞ በመጪው ሃምሌ በካይሮ ስብሰባ ለማድረግ መስማማታቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በትምህርት፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስልጠና እንዲሁም በግብርና ሥራ ላይ ለመተባበርም ተስማምተዋል።

እስካሁን የግብጽ ባለሃብቶች 900 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ ፈሰስ በማድረግ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰማርተዋል ያሉት አምባሳደሩ፤ ተሳትፏቸውን ለመጨመር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይም ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

በሚያዚያ 2015 በሊቢያ በረሃ ላይ አይ ኤስ በተባለው ቡድን የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ሌላኛው የመወያያ ርዕስ ነበሩ። የኢትዮጵያውያኑን አጽም ካለበት ፈልጎ ማግኘት እና ቅሪታቸው ወደ ሃገር ቤት እንዲመለስ የማድረጉን ሥራ ማስጀመር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን አምባሳደሩ ጨምረው ተናግረዋል።

”በትክክለኛ መስመር ላይ ያለ ጉዳይ ስለሆነ በጠንካራ ሥራ እና ብርታት፤ እልባት እንደሚያገኝ ተስፋችን የበረታ ነው” በማለት ያላቸውን እምነት አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በግብጽ ውስጥ የሚኖሩ እና በተለያዩ ምክንያቶች እስር ቤት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተወያዩበት እንደሆነ አምባሳደር ታዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቅን በሚባሉ ጉዳዮች ለብዙ ዓመታት በፍርድም ሆነ ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ የቆዩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የገለጹት አምባሳደሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፤ 32 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሌሊቱን ሙሉ መጓጓዣ ሰነዳቸው ሲዘጋጅ ቆይቶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ሃገራቸውን ጥለው በግብጽ የተቀመጡ ዜጎች አሉ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወኑ ባሉ የተለያዩ የልማት መስኮች መሳተፍ እንፈልጋለን ያሉትም ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ወደ ኤርትራ መግባት ቀላል ሊሆን ይችላል፤ መውጣት ግን እጅግ ከባድ ነበር ያሉት” አምባሳደሩ ከብዙ ጥረት በኋላ ወደ ግብጽ መምጣታቸውን ይናገራሉ።

እነዚህን ሰዎች ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ምን ዓይነት ድርድር ተደርጎ ነበር ተብለው የተጠየቁት አምባሳደሩ፤ መንግስት ምንም አይነት ድርድር ውስጥ እንዳልገባ እና ኢትዮጵያውያኑ ራሳቸው ወደ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት በመምጣት ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ ገልጸዋል።

ግብጽ ውስጥ 6000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩ ሲሆን አብዛኛዎቹም ሴቶች ናቸው።

እነዚህ ሴቶች የተሰማሩበትም የሥራ መስክ የቤት ሠራተኝነት፤ የልጅ ተንከባካቢነት እና በሱቆች ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት እንደሆነ አምባሳደር ታዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.