NEWS: ጣሊያን በስደተኞች ላይ ጨከነች

ጣሊያን የስደተኞች ነገር አንገፍግፏታል። 629 ስደተኞችን የጫነች መርከብ ማልታና ጣሊያን ጠረፍ ላይ ሆና በከንቱ እየዋለለች ነው።

ከተሳፋሪዎቹ 123ቱ ከ18 ዓመት በታች ሲሆኑ ከኤርትራ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ሱዳን የመጡ ናቸው ተብሏል። ሰባት ነፍሰ ጡሮች በመርከቧ ውስጥ ይገኛሉ።

የቀኝ አክራሪው መሪና የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ማቴዎ ሳልቪኒ “ከዚህ በኋላ ወደቦቻችን ለስደተኞች ዝግ ናቸው። ከፈለገች ማልታ ትቀበላቸው” በሚል ነገሩን ወደ ጎረቤት አገር ገፍተውታል።

629 ስደተኞችን ያዘለችው አኳሪያስ የተሰኘችው ይህቺ መርከብ የበላይ ትዕዛዝ እስኪመጣ “ባለሽበት እርጊ” ተብላለች። ማራገፍም መንቀሳቀስም አልቻለችም።

ማልታ በበኩሏ “ይህ ጉዳይ እኮ እኛን አይመለከትም። ስደተኞቹ በጣሊያን ሉአላዊ ግዛት ውስጥ ነው የሚገኙት” ብላለች።

ከተለያዩ ጀልባዎች በሕይወት አድን ድርጅቶች አማካኝነት ተሰብስበው ወደ አኳሪየስ መርከብ የገቡት የእነዚህ ስደተኞች እጣ ፈንታ አነጋጋሪ ሆኗል።

ስደተኞችን ያሳፈረችው አኳሪየስ ወደ ጣሊያን የወደብ ከተሞች በማምራት መልህቋን ለመጣል ስላልተፈቀደላት በሜዲትራኒያን ዳርቻ እየተንከላወሰች ትገኛለች።

ምክንያቱም ደግሞ የጣሊያን የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ መርከቧን በጣሊያን ወሽመጥ ድርሽ እንዳትል በማለታቸው ነው።

ጣሊያን ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለሚመጡ ስደተኞች የመጀመርያዋና ተመራጯ መዳረሻ ናት።

ሳልቪዮኒ የሚመሩት ሊግ የተሰኘው የቀኝ አክራሪ ፓርቲ በቅርቡ ለጣሊያዊያን መራጮች ቃል እንደገባው በስደተኞች ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፊቱን እንደሚያዞር ተናግሮ ነበር።

“ዓላማችን የ629 ስደተኞችን ነፍስ መታደግ ነው። ግማሾቹ ትናንት ከሞት አፋፍ የተመለሱ ናቸው።” ብለዋል፣የኤስ ኦ ኤስ በጎ አድራጊው ድርጅት ቃል አቀባይ ማቲለድ አቪሊያን።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ በበኩሉ በጉዳዩ እጃቸውን ያስገቡ አገሮችም ሆኑ ድርጅቶች በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጡ አሳስቧል። አኳሪየስ መርከብ ስደተኞቹን እንድታራግፍ ሊፈቀድላት ይገባል” ብለዋል።

ስደተኞቹን መጀመርያ በሕይወት የታደጉት የጣሊያን የባሕር ኃይል አባላት፣ የጣሊያን ጠረፍ ጠባቂዎችና የንግድ መርከቦች ሲሆኑ ከዚያ በኋላ ግን ሁሉም ስደተኞች አኳሪየስ የተሰኘችው መርከብ ውስጥ እንዲሳፈሩ ሆነዋል።

አሁን አኳሪየስ መርከብ ውስጥ ከሚገኙት ውስጥ 123ቱ ከ18 ዓመታ በታች ሲሆኑ፣ 11 ብላቴናዎች እና ሰባት ነፍሰ ጡሮች ይገኙበታል።

ዕድሜያቸው ከ13-17 የሚሆኑት ወጣቶች ደግሞ በአብዛኛው ከኤርትራ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ሱዳን የመጡ ናቸው።

አንድ የአካሪየስ መርከበኛ እንዳለው መርከባቸው ወዴት መሄድ እንዳለባት ከበላይ ትዕዛዝ እስኪመጣ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ትናንት ከደረስንላቸው ስደተኞች መሐል 50 የሚሆኑት በመስጠም ላይ እያሉ ነው የታደግናቸው ብሏል።

በዚህ አጣብቂኝ መሐል የጣሊያኑ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሳልቪኒ እንደሚሉት ግን ጣሊያን ለስደተኞች በሯን ዘግታለች።

” ማልታ አንድም ስደተኛ አልተቀበለችም፣ ፈረንሳይ ስደተኞችን ወደ ድንበር ትገፋለች፣ ስፔይን ድንበሯን በጦር መሣሪያ ትጠብቃለች። እኛ ምን እዳ አለብን?” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ደግሞ “ሮም ስደተኞችን ወደመጡበት መመለስ ትጀምራለች። የቀሩትን ደግሞ ለሌሎች የአውሮፓ አገሮች ታድላለች” ብለዋል።

ይህ ሐሳብ ግን በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ድጋፍ አላገኘም።

ሳልቪኒ ስደተኞችን የሚታደጉ ነፍስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅቶችን “የስደተኛ ንግድ ሸሪኮች” ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.