BBC: ‹‹እነ ቴሌን ለግል ባለሀብት?›› ታሪካዊ ስህተት ወይንስ መልካም አጋጣሚ ?

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ ካስተላለፋቸው አበይት ውሳኔዎች አንዱ በመንግስት እጅ ውስጥ የቆዩ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ለግል ባለሃብቶች እንዲዘዋወሩ መፍቀድ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ለዓመታት ‹በግል ባለሀብቶች እጅ ሊገቡ አይገባም› በሚል መንግስት ሲሟገትላቸው የባጁትን ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች እና የባህር እና ሎጂስቲክ ባለስልጣንን በሙሉ ወይንም ‹በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ› ወስኗል፤ይሄ ውሳኔ ከተሰማ በኃላ የድጋፍ እና ነቀፌታ ሀሳቦች ተከትለዋል፡፡

ቢቢሲ ባናገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዘንድም ጉዳዩ ለየቅል የሆነ አቀባባል እንዳለው ለማጤን ችሏል፡፡ በመንግስት እጅ ውስጥ የቆዩ የንግድ ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ጽንሰ ሀሳብ በፖሊሲ ደረጃ ከተያዘ ሃያ ዓመታት ግድም እንዳለፉት የሚጠቅሱት የአግሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ደምስ ጫንያለው፣ የአሁኑ የመንግሥት እርምጃ ልዩ የሆነው ግዙፍ የንግድ ተቋማት ለግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ክፍት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

‹‹ለኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ክፍት መደረጋቸው ትልቅ እመርታ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች (እንደ ኢትዮቴሌኮም) ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ከፍተኛውን የሀብት ድርሻ ኢትዮጵያዊያን እንዲይዙት ማድረግ ቢቻል ትልቅ ለውጥ ነው›› የሚሉት ዶ/ር ደምስ ውሳኔው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲጠናከሩ እገዛ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ፡፡ ብዙ ባለሀብቶቻችን ይሄን መሳይ ‹የኢንቨስትመንት› አማራጭ ስላልነበራቸው የባንክ ሼርን መግዛትን በመሰሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተጠምደው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሃላፊ እና በአሁኑ ጊዜ ‹ኢንሺየቲቭ› አፍሪካ የተሰኘው ተቋም መስራች እና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክብር ገና ግን ፈላጊ ያላቸው፣ ትርፍ እያስገኙ ያሉ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶችን ለግል ባለሀብቶች ማስተላላፍ ትልቅ ጉዳት እንዳለው ይሟገታሉ፡፡ ለአብነት የሚጠቅሱት ጉዳት ደግሞ፣ ለልማት ስራዎች ማስፈጸሚያ ይውል የነበረው የንግድ ድርጅቶቹ ገቢ ለባለሀብቶች ግላዊ ብልጽግና ብቻ ሊውል የመቻሉን ዕድል ነው፡፡

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.