NEWS: የኢትዮ- ሕንድ የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ በኒው – ዴልሂ ተካሄደ

ኢትዮጵያና ሕንድ ሁለተኛውን የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ በኒውዴልሂ ሕንድ ተካሂዷል፡፡
የኢፌ.ዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሽማ ስዋራጅ ጋር ምክክር ካደረጉ በኋላ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀው ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሮ የሕዝቦቻችንን ጥቅም በዘለቄታዊነት ማረጋገጥ እንዲቻል ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነት እንደምትሠራ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም ሁለቱ ሀገራት ለዓለም ሰላምና ደህንነት አስተዋፅኦ ከማድረግ ባሻገር በሀገራቱ መካከል ኢንቨስትመንትና ንግድን በማስፋፋት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትብብር በማሳደግና አቅም ግንባታን በማጎልበት የሕዝቦቻቸውን የጋራ ጥቅም በማራመድ ረገድ ውጤታማ ተግባራትን አከናዋነዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሕንድ መንግሥት ለስኳር ኘሮጀክቶች፣ ለኢትዮ-ጅቡቲ ኤሌክትሪክ መስመርና ለመቐለ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሃይል አቅርቦት የሚውል ብድር (LoC) በመፍቀድ ስላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በፀረ ሽብር ትግል፣ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ሪፎርምን የአየር ንብረት ለውጥን በመሳሰሉ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በያዝነው ዓመት የሕንድ ኘሬዝዳንት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ፍሬያማ ውይይቶች የተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው በወቅቱ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን እንዲሁም የንግድ ስምምነቶች መፈረማቸው አወንታዊ እርምጃዎች እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡
የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሽማ ስዋራጅ በበኩላቸው የጋራ ኮሚሽኑ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የጋራ ዕሴቶችን መሠረት ባደረገውና ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የኢትዮጵያና ህንድ ጠንካራ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ጥቅሞች ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የፖለቲካ፣ የንግድና የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በማተኮር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ፤ ለአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗን ጠቅሰው ሁለቱ ሀገራት የደቡብ – ደቡብ ግንኙነት በማጠናከር ለሰላምና ደህንነት እንዲሁም ለልማትና ለዕድገት በሁለትዮሽም ሆነ በባለ-ብዙ ወገን መድረኮች ላይ በጋራ መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ በአህጉሩ፣ በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በኢጋድ አባላት ከፍ ያለ ሚና ለሰላም መስፈን የምታበረክተውን አስተዋጽኦ ሀገራቸው እንደምትገነዘብና ለዚህም አድናቆት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሕንድ መንግሥት ኢትዮጵያ ለልማት ለምታደርገው ጥረት በሁሉም መስኮች እገዛው እንደሚቀጥል ገልፀው መግንሥታቸው በኢትዮጵያ ለሚሠማሩ ኢንቨስተሮችና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ባሁኑ ወቅት ከ500 የሚልቁ የሕንድ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሠማርተዋል፡፡

በንግድ ዘርፍ የታየው ዕድገት አበረታች ቢሆንም የንግድ ሚዛኑን በማስተካከል ረገድ ሀገራቱ ያላቸውን ዕምቅ ሃብት በመጠቀም ተጨማሪ ጥረቶች ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
በዚሁ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሠልጠኛ ተቋምና በሕንዱ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ተቋም መካከል የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመ ሲሆን ቀደም ሲል የተፈረሙ ሌሎች ስምምነቶች በተሟላ ሁኔታ በተግባር ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ሁለቱም ወገኖች በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሕንድ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረቱበትን 70ኛ ዓመት በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

ምንጭ:  Amhara Mass Media Agency

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.