NEWS: የዶናልድ ትራምፕ ከኢራኑ ስምምነት ማፈንገጥ ዓለምን እያነጋገረ ነው

ትራምፕ “የበሰበሰና የተላ” በሚሉ ጠንካራ ቃላት ያወገዙትን የኢራኑን ስምምነት ቀዳደው እንደሚጥሉት መዛት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

የአውሮፓ አጋሮቻቸው እርሳቸውን ለማግባባት ባለፉት ሳምንታት ዋሺንግተን ደጅ ጠንተዋል።

በተለይም የፈረንሳዩ ማክሮን፣ የትራምፕን ሐሳብ ለማስቀየር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።

የጀርመኗ መርሂተ መንግሥት አንጌላ መርከል፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሚቻላቸውን ሁሉ ጥረዋል።

ትራምፕ ግን ለማንም አልተመለሱም።

በአውሮፓውያኑ 2005 ከተፈረመው የኢራኑ የኒክሊየር የጋራ ስምምነት መውጣታቸውን ትናንት ምሽት በይፋ አስታውቀዋል።

ባለሥልጣኖቻቸውንም በኢራን ላይ ጠበቅ ያሉ ምጣኔ ሐብታዊ ማዕቀቦችን እንዲጥሉ መመሪያ ሰጥተዋል።

ኢራን በምላሹ ዩራኒየም የማበልጸጉን ሥራ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው ብላለች።

ሐሰን ሩሃኒ “አሜሪካ የገባችበትን ስምምነት ለማክበር ባለመፍቀዷ የአቶሚክ ኃይል ድርጅታቸው ዩራኒየም የማበልጸጉን ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እንዲያደረግ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።

ሩሃኒ እንደሚሉት ለጥቂት ሳምንታት ሌሎች የስምምነቱ ፈራሚ አገራት ጋር ለመነጋገር ስንል “ልንታገስ እንችላለን” ይላሉ።

“የስምምነቱን ዓላማዎች ከሌሎች ፈራሚ አገራት ጋር ተደራድረን መስማማት ከቻልን ስምምነቱ ውስጥ ለመቆየት እንችላለን” ሲሉም ተስፋ ሰጥተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል የስምምነቱን ጎዶሎነት አጉልተው ሲተቹ ነበር።

ስምምነቱ ኢራን የኑክሌየር መሣሪያ እንዳታመርት የሚያግዳት ለተወሰኑ ዓመታት ብቻ መሆኑ፣ የባሊስቲክ ሚሳይል እንዳታመርት አለመከልከሉ፣ የመቶ ቢሊየን ዶላር ያልተጠበቀ ገቢ ለኢራን ማስገኘቱን የስምምነቱ ሕጸጾች እንደሆኑ በመግለጽ ይተቻሉ።

ይህንን “ድንገቴ” ገንዘብ ኢራን መካከለኛው ምሥራቅን ለማተራመስ ትጠቀምበታለች ይላሉ ትራምፕ።

ኢራንን የኒክሊየር ቦንብ እንዳታመርት” በዚህ በበሰበሰና በተላ ስምምነት ልናቆማት እንደማንችል ግልጽ ሆኖልኛል” የሚሉት ትራምፕ ባልተጠበቀው የተናጥል ውሳኔያቸው ዓለምን እያነጋገሩ ነው።

ይህን ስምምነት እውን እንዲሆን ብዙ የጣሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የትራምፕን ተግባር “የተንሸዋረረ” ብለውታል።

ኢራን የኑክሌር እንቅስቃሴዋን የገታቸው የማዕቀብ እፎይታውን ተከትሎ ነበርImage copyrightGETTY IMAGES
አጭር የምስል መግለጫኢራን የኑክሌር እንቅስቃሴዋን የገታቸው የማዕቀብ እፎይታውን ተከትሎ ነበር

ማዕቀቡ መቼ ተግባራዊ ይሆናል?

የምጣኔ ሐብቱ ዕቀባ ተግባራዊ ለመደረግ ከ90 እስከ 180 ቀናት ሊወስድ ይችላል።

በ2015 የተፈረመው ስምምነት ያስወገዳቸውና በተለይም በኢራን የነዳጅ ምርት፣ በአውሮፕላን የውጭ ንግድ፣ በብረት ንግድ እንዲሁም የኢራን መንግሥት የአሜሪካንን ዶላር ለመግዛት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ አዲሱ ማዕቀቡ ክንዱን ያሳርፋል።

የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተን እንዳሉት ከኢራን ጋር በንግድ የተሳሰሩ የአውሮፓ ኩባንያዎች የንግድ ትስስራቸውን ከ6 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሊያጠናቅቁ ግድ ይላቸዋል።

አለበለዚያ ግን የአሜሪካ ማዕቀብ ለነርሱም አይመለስም።

መሪዎች በጉዳዩ ዙርያ ምን አሉ?

የስምምነቱ ፈራሚዎች ከሆኑት የአውሮፓ አገራት ውስጥ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ በአሜሪካ ውሳኔ ማዘናቸውን ገልጸዋል። የራሺያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “እጅግ አሳዛኝ ውሳኔ” ሲሉ የትራምፕን የተናጥል ተግባር ተችተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ፌዴሪካ ሞጋሪኒ ኅብረቱ ለኑክሌር ስምምነቱ አሁንም ተገዢ እንደሆነና ስምምነቱንም እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

ባራክ ኦባማ በበኩላቸው በፌስቡክ ገጻቸው እንደጻፉት ስምምነቱ የአሜሪካንን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደነበር ተከራክረዋል።

“ከዚህ ስምምነት ማፈንገጥ የአውሮፓ አጋሮቻችንን የመካድ ያህል ነው። ይህ ስምምነት የአሜሪካ ታላላቅ ዲፕሎማቶች፥ ሳይንቲስቶች፥ የደኅንነት ሰዎችና ባለሞያዎች ተደራድረው የደረሱበት ጥሩ ስምምነት ነበር” ብለዋል።

“ከሰሜን ኮሪያ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ሥራ እየደገፍን ባለንበት ሰዓት ከኢራን ስምምነት ማፈንገጥ የምንፈልገውን ውጤት የሚያሳጣን ነው የሚሆነው” ሲሉም የትራምፕን ውሳኔ ተችተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዋና ጸሐፊው ቃል አቀባይ እንደተናገሩት “አንቶኒዮ ጋተረስ የትራምፕ ውሳኔ እጅግ አሳስቧቸዋል” ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል። ሌሎች ተፈራራሚዎች ግን በስምምነቱ እንዲቀጥሉ ዋና ጸሐፊው መማጸናቸውንም ጨምረው አስገንዝበዋል።

በተቃራኒው የእስራኤሉ ቤንያሚን ናታኒያሁ የትራምፕን ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ አሞካሽተዋል። ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።

የኢራን ባላንጣ የሆነችው ሳኡዲ አረቢያ በበኩሏ የትራምፕ ውሳኔን በሙሉ ልብ እንደምትደግፈው ገልጻለች።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

7 Comments

Comments are closed.