የተሰበረ አጥንት ቶሎ እንዲያገግም በቤት ውስጥ ልከናወኑ የሚገቡ ተግባራት – Homemade Remedies To Heal Broken Bones

ስብራት በጣታችን፣በክንዳችንም ይሁን በታችኛው የእግራችን ክፍል ሲያጋጥመን መዳኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ባለመዳኑ ምክንያት ውስብስብ የጤና ችግር አስከትሎ እንቅስቃሴና አቅማችንን የሚገድብ ይሆናል፡፡
የተሰበረ አጥንት የሚያገግምበት ጊዜ እንደ እድሜያችን፣ ጤንነታችን፣ አመጋገባችንና እንደ ጉዳቱ ደረጃ የሚወሰን ቢሆንም የአጥንት ሀኪም የሚሰጠውን መመሪያ መከተል ደግሞ ዋነኛ ቁም ነገር ነው፡፡
የተሰበረ አጥንት ቶሎ ማገገም የሚችልባቸው ነጥቦች ተብለው የተለዩት፡-
1. ሲጋራ ማጨስ ማቆም
ሲጋራ የደም ዝውውር በደንብ እንዳይከናወን ስለሚያደርግ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ወደ ተጎዳው አጥንት እንዳይደርስ ያደርጋል። ስለሆነም ስብራት ካጋጠሞት የማጨስ ልምድን ማቋረጥ ቶሎ ለማገገም ይረዳል፡፡
2. አልኮልን ማስወገድ
ባለሙያዎች እንደሚሉት አልኮል መውሰድ ስብራት ቶሎ እንዳያገግም ያደርጋል። ምክንያቱም ሰውነታችን የተጎዳው አጥንት እንዲያገግም የሚሰራው ስራ በአልኮሉ አማካኝነት የተጎዳው አጥንት ጋር እንዳይደርስ ስለሚያደርግና አዳዲስ የሚፈጠሩ የአጥንት ሴሎችን እድገት ስለሚገታ ነው።
3. ቡናና መሰል የካፌን መጠጦችን ማስወገድ
ቡናና ሻይ እንዲሁም ለስላሳ መጠጦችን አለመጠቀም። ምክንያቱም ካፌይን ነክ መጠጦች ለአጥንት ጥንካሬ የሚረዳው ካልሽየም የተሰኘው ማእድን በኩላሊታችን አማካኝነት ከሰውነታችን እንዲወገድ ስለሚያፈጥን ነው፡፡
4. በቂ የካልሽየም ይዘት ያላቸውን ምግቦች መውሰድ
የካልሽም ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነና ለአጥንት ግንባታ ጠቃሚ የሆኑ እንደ ወተት፣ እርጎ፣ አኩሪ አተር፣ አረንጓዴ ተክሎች፣ ሳርዲን፣ ጥራጥሬዎችንና የብርቱካን ጭማቂ መጠቀም፡፡ ምግቦቹን እንደ ልብ ማግኘት ካልቻልን የካልሽም ሰፕልመንት በጥንቃቄ መውሰድ ፡፡

5. በካሎሪና በፕሮቲን የበለፀጉ ምግቦችን መውሰድ
ሰውነት ሲጎዳ የሚወሰደው የካሎሪ መጠን ሊጨምር ይገባል። ባለሙያዎች እንደሚሉት የተሰበረ አጥንትን ለመጠገን በቀን እስከ 6ሺህ ካሎሪ ድረስ ያስፈልጋል፡፡ በምግብ ውስጥ በቂ ፕሮቲን ማካተትም ይገባል፡፡
6. የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
የተለያዩ ቫይታሚንና ሌሎች ንጥረነገሮችን አመጣጥኖ መመገብ በአካል ላይ የደረሰ ጉዳት በተለይ እንደ ስብራት ካሉት ማገገም እንዲቻል ይረዳል። ፍራፍሬዎችንና አትክልትን በብዛት መጠቀምም ይመከራል፡፡
7. እንቅስቃሴ ማድረግ
እንቅስቃሴ ማድረግ የደም ዝውውርን በማፋጠን ምግብና ኦክስጅን ወደ ተጎዳው አካል በቀላሉ እንዲደርስ ያደርጋል። ነገር ግን እንቅስቃሴው ስብራቱን ለበለጠ ጉዳት እንዳይዳርግ የሃኪም ምክር ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.