የታንዛኒያ መንግሥት ጦማሪያን እንዲመዘገቡ አዘዘ

                  

የታንዛኒያ የኮሚዩኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በሃገሪቱ ያሉ ጦማሪያንና የድረ-ገፅ ባለቤቶች ሕጋዊ ሆነው ለመስራት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲመዘገቡ አዘዘ።

ይህ ባለፈው ወር በመንግሥት ተግባራዊ የሆነውን አወዛጋቢውን አዲስ ህግ ተከትሎ ፅሁፎችን ለመቆጣጠር ባለስልጣናት የወሰዱት ተጨማሪ እርምጃ ነው።

ይካሄዳል ለተባለው ምዝገባ በኢንተርኔት የድምፅና የቪዲዮ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ሰዎችን ጨምሮ ሁሉም የድረ-ገፅ ባለቤቶችና ጦማሪያን አንድ ሺህ ዶላር ያህል መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

በተጨማሪም ሁሉም ተመዝጋቢ የተከለከሉ ይዘቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራርን መዘርጋት ሲኖርባቸው፤ የተጠቃሚዎችን የመታወቂያ ካርድ ዝርዝርና የኢንተርኔት አድራሻን ጨምሮ ሌሎች መረጃንም መዝግቦ የመያዝ ግዴታ አለበት።

ይህንን ደንብ ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ሰው እስከ ሁለት ሺህ ዶላር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ወይም ከአንድ ዓመት ባላነሰ የእስር ቅጣት ወይም በሁለቱም ሊቀጣ ይችላል።

ይህን እርምጃ በርካታ የመብት ተሟጋቾች፣ የድረ-ገፅ ይዘት አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች፤ መንግሥት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት ለመጫን ይጠቀምበታል በማለት እየከሰሱ ነው።

ነገር ግን መንግሥት ይህንን እርምጃ የወሰደው ሀገሪቱን ከሀገር ውስጥና ከውጪ ከሚመጡ ያልተፈለጉ የድረ-ገፅ ይዘቶች ለመከላከል እንደሆነ ይናገራል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement