95 በመቶው የአለም ህዝብ የሚተነፍሰው አየር የተበከለ ነው – ጥናት

                   

የአለም ህዝብ ከሚተነፍሰው አየር 95 በመቶው ጤነኛ ያልሆነና የተበከለ ሲሆን፥ የችግሩ ተፅዕኖ በደሃ ሀገራት ጎልቶ እንደሚታይ አንድ ጥናት አመለከተ።

በፈረንጆንቹ 2016 ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ የ6 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ነው ሪፖርቱ ያመለከተው። 

የአየር ብክለት በስትሮክ፣ ልብ በሽታ፣ በከባድ ሳንባ በሽታና ካንሰር እንዲሁም በሌሎች በሽታዎች ለሚከሰት ሞት ዋና ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል። 

እንደ ሪፖርቱ የአየር ብክለት ከከፍተኛ የደም ግፊት፣ ስኳር እና ሲጃራ ማጨስ ቀጥሎ ለሞት ምክንያት በመሆን በአራተኛ ደረጃ ይገኛል።
ይህ የአየር ብክለት ለመተንፈሻ አካላት በሽታ ምክንያት በመሆኑ ወጣቶችና ጎልማሶች በስራና በትምህርት ገበታቸው እንዳይገኙ ምክንያት ከመሆን አልፎ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ችግሩን ለመከላከል አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥምም የአየር ብክለት የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ጥሩ ውጤት እየታየ ነው ተብሏል። 

በሪፖርቱ መሰረት በአለማችን ከአየር ንብረት ብክለት ጋር ተያይዞ ለሚከሰት 50 በመቶው ሞት ቻይናና ህንድ ዋነኞቹ ተጠያቂዎቹ እንደሆነ ተገልጿል።

በህንድ ከአየር ብክለት ጋር ተያይዞ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ህፃናት በፈረንጆቹ 2016 ህይወታቸው እንዳለፈ ተጠቁሟል። 

ቻይና በአሁኑ ወቅት የአየር ብክለትን በመቀነስ በኩል ለውጥ እያመጣች እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሌሎች ሀገራትም ይህ ለውጥ እየታየ መሆኑ ታውቋል።

በቤት ውስጥ ለምግብ ማብሰያነትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉት ከሰልና እንጨት በቤት ውስጥ ለሚከሰት አየር ብክለት ምክንያት እንደሆኑ ተነግሯል።

በዚህ የተነሳ በደሀ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች በቤት ውስጥና በውጭ ላለው የአየር ብክለት እንደሚጋለጡ ሪፖርቱ ያሳያል።

በህንድ ከአራቱ ሰዎች አንዱ እና በቻይና ከአምስቱ አንዱ በሁለቱ አየር ብክለት ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ነው የተነገረው። 

የአለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2017 ባወጣው ሪፖርት በአየር ብክለት ምክንያት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ህፃናት አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ህይወታቸው እንዳለፈ አስታውቋል።

በአየር ብክለት ምክንያት ተፅዕኖ ከሚደርስባቸው መካከል 92 በመቶዎቹ በደሀ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement