በአማራ ክልል ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት ለሚሄዱ ሰዎች የቅድመ ጉዞ ስልጠና መስጫ ማእከላት ተቋቋሙ

                  

ዙፋን ካሳሁን

በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ ለሚሄዱ ሰዎች የቅድመ ጉዞ ስልጠና የሚሰጥባቸው ማእከላት ማቋቋሙን የአማራ ክልል ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳውቋል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አበጀ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ማእከላቱ የተቋቋሙት ባህርዳር እና ደሴ ላይ ነው።

ለዚህም ተጓዞች ወደ እነዚህ ማእከላት ገብተው ከሚያገኙት የቅድመ ጉዞ ስልጠና በፊት በሶስት መስኮች ላይም ክልሉ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ስልጠና እየተሰጠባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች መካከልም የቤት አያያዝ፣ የህፃናት እና አረጋውያን እንክብካቤ የሚሉት የሚገኙበት መሆኑንም አስታውቀዋል።

ቢሮው በህጋዊ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት ለሚሄዱ ሰዎች ስልጠናዎችን ከመስጠት ጎን ለጎንም ህገ ወጥ ስደትን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎችንም እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement