እስራኤል ረጅሙን የጋዛ ዋሻ አፈረሰች

               

ከጋዛ ሰርጥ ወድ እስራኤል የሚወስድው እና በሽምቅ ተዋጊዎች የተቆፈርውን ዋሻ የእስራኤ ጦር ከጥቅም ውጪ ማድረጉን አስታወቀ።

የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር አቪጎር ሊበርማን እንዳሉት ይሄኛው እስራኣኤል ከደረሰችባቸው ሁሉ ረጅሙ እና በጣም ጥልቁ ዋሻ ነው።

ዋሻው በ2014 ከተካሄደው የጋዛ ጦርነት ጀምሮ እንደተቆፈረ እና በጊዜውም እስራኤል ከ 30 በላይ የሚሆኑ ዋሻዎችን ማፈራረሷን አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ ከሆነ፤ ዋሻው በሃማስ የተቆፈረ እንደሆነና በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ጃባሊያ አካባቢ የተጀመረ ነው። ዋሻው በናሆል ኦዝ አቅጣጫ ጠቂት የማይባሉ ሜትሮች ወደ እስራኤል እንደገባና መውጫ ግን ገና እንዳልተሰራለት ኮሎኔል ጆናታን አክለዋል።

ዋሻው ወደ ጋዛ በብዙ ኪሎሜትሮች የተዘረጋ ሲሆን፤ ከሌሎች ዋሻዎችም ጋር የተገናኘና ጥቃት ለመፈጸም ምቹ ነበር ነው ብለዋል።

እስራኤል በሳምንቱ መጨረሻ ነው ዋሻውን ከጥቅም ውጪ ያደረገችው። ቃል አቀባዩ ሲናገሩም ”ዋሻው ለረጅም ጊዜ ጥቅም እንዳይሰጥ በሚያደርግ መሳሪያ ሞልተነዋል” ብለዋል።

በቅርብ ወራት ውስጥ እስራኤል ካፈራረሰቻቸው የጋዛ ዋሻዎች መካከል ይህ አምስተኛው ነው።

አንዳንዶቹ ዋሻዎች በፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ታጣቂ ቡድን የተሰሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጋዛን በተቆጣጠረው የሃማስ እስላማዊ ቡድን የተቆፈሩ ናቸው።

ከባለፈው አመት ጀምሮ እስራኤል ዋሻዎችን መለየት የሚችል ልዩ መሳሪያ እየተጠቀመች ሲሆን በአሁኑ ሰአት ደግሞ በአዋሳኟ ጋዛ በኩል የሚቆፈሩ ዋሻዎችን ለማስቆም በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተራቀቀ የምድር ውስጥ መከላከያ እየገነባች ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement