መንግስት የሃገሪቱን ሰላም ይበልጥ በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ይሰራል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ

                     

መንግስት የሃገሪቱን ሰላም ይበልጥ በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ መንግስት የሃገሪቱን ሰላም ይበልጥ በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ባለፉት አመታት ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ሃገሪቱ ችግር ውስጥ ገብታ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ችግሩ በህዝቦች አብሮ የመኖርና የአንድነት ባህል መቀረፉን ጠቅሰዋል።

በንግግራቸው የሃገሪቱ ሃብት ህዝቦቿ መሆኑን ጠቅሰው በሰላም እጦት ምክንያት በህዝቦች መካከል መቃቃር ተፈጥሮ የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይገታ፥ ሁሉም በሃገራዊ ሃላፊነት ለሃገሩ ዘብ እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለኢኮኖሚው እድገት እንቅፋት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍም ጠንካራ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

የማምረቻ ዘርፉን ማጠናከርና በተለይም የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን አቅም በማጠናከር ምርቶችን በማብዛት ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለውጭ ምንዛሪ ብክነት ምክንያት እየሆኑ ባሉ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል በማድረግ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም አስረድተዋል።

መንግስት አሁን ላይ በህዝቡ ዘንድ የታየውን ተስፋ እውን ለማድረግ በጽናት እንደሚሰራ ጠቅሰው፥ ህዝቡም ባለፉት አመታት በአንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመካስ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ቅሬታዎችን ለመፍታትም የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰና ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚጠየፍ ሰራተኛ ለመፍጠር ይሰራል ነው ያሉት።

በተቋማት የሚደረገው ምደባ ዕውቀትና ክህሎትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ጠቅሰው፥ በዚህም የመንግስት የማስፈጸም አቅም ይሻሻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በተንዛዛ ስብሰባ የሚባክን ጊዜና ሃብትን ለማስቀረትና የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የታገዘ መንግስታዊ አሰራር እንዲኖር እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ከትምህርት ጋር ተያይዞም የትምህርት ጥራት ላይ ያተኮረ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የየትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጥረት እንደሚደረግም አውስተዋል።

በመስኖ ልማት፣ በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች እንዲሁም ታዳጊ ክልሎች ድጋፍ በማድረግ ዘርፉን የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት።

በዲፕሎማሲው መስክም መርህን መሰረት ያደረገ መልካም ግንኙነት በተለይም ከአፍሪካውያን ሃገራት ጋር በመመስረት፥ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምንጫወተውን ሚና አጠናክረን እንቀጥላለምን ብለዋል ዶክተር አብይ።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲጎለብት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጠናከር እንደሚኖርባቸው ጠቅሰው፥ ቀጣዩን ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ታማኝ ለማድረግ መንግስት በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የፍትህ ስርዓቱ ላይ ለውጡ የሚያመጡ የመፍትሄ እርምጃ እንደሚወሰድ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ስርዓቱ የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳና ህዝቡ ትክክለኛ ፍርድ የሚያገኝበት እንዲሆን እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ከዚህ ባለፈም ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ አንዳንድ ህጎች ላይ ማሻሻያ እንደሚኖር ጠቅሰዋል።

የፀጥታና የደህንነት ተቋማትም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚጠብቁ እንዲሆኑ ይሰራል ሲሉም በመልዕክታቸው አንስተዋል።

የሚዲያ ተቋማትም በሃገር ግንባታ፣ ሰላም እና ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ እንዲሁም ከወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሃይማኖት መሪዎችም ትውልድ በመቅረጽ፣ ሰርቆ የመክበር አካሄድን እና ሙስናን በማውገዝ፥ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እሴቶችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንዲሁም መምህራን ትውልድን በመቅረጽ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ ወጣቶች የሃገሪቱ የለውጥ አንቀሳቃሾች መሆናቸውን ተረድተው ለሃገር እድገትና ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ካለፉ ታሪኮች ለሃገር እድገትና ግንባታ የሚበጀውን በመውሰድ መስራት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በወጣትነት ያለውን ልዩ ሃይል ሃብት ለማፍራትና ሃገራዊ እድገት ለማምጣት መጠቀም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አካል ጉዳተኞችን በሚደረገው ሃገራዊ የሃገር ግንባታ በማሳተፍም ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ይሰራል ብለዋል።

በመጨረሻም መላው የሃገሪቱ ህዝቦች ለሰላምና ሃገራዊ አንድነትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ዘብ በመቆም የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ለማሳደግ ሊሰሩ እንደሚገባም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement