በአንድነትና በመተሳሰብ ስሜት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ እናደርጋለን – አስተያየት ሰጪዎች

               

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2010 በአንድነትና በመተሳሰብ ስሜት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በሚሊኒየም አዳራሽ የተገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማምሻውን 25 ሺህ ከሚሆኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ ይወያያሉ።

በአዳራሹ የተገኙት የውይይቱ ተሳታፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የስራ ዘመን ስኬታማ እንዲሆን በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፏቸው ነው የገለጹት።

የመዲናዋ ነዋሪ አቶ አማኑኤል ሙላቱ ባለፉት ጊዜያት አገሪቷ ሁከትና አለመረጋጋት ውስጥ ገብታ እንደነበረ አስታውሰው በተደረገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ወደ ቀድሞ ሰላሟ እየተመለሰች ነው ብለዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርም የገቡትን ቃል ለመፈጸም በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት ይጠበቅባቸዋል ካሉ በኋላ እርሳቸውም በሚችሉት አቅም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዘነበች ወልደሰማያት የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውንና በአዳራሹ ውስጥ ያለውም ድባብ ይህንኑ እንደሚያንፀባርቅ ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአንድነት በመቆም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ያሉት ወይዘሮዋ እርሳቸውም ለዚህ ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች የሚሰጡትን ምላሽ ለማድመጥ መጓጓታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ለታ ተመስገን ናቸው።

እርሳቸውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዘመን ስኬታማ እንዲሆን እንደ ዜጋ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህብረተሰቡ ተወካዮች ጋር የሚያደርጉት ወይይት “የፍቅርና የአንድነት ኪዳን” የሚል መሪ ሃሳብ የተሰጠው ሲሆን፤ አንድነትና የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጎልበት ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ተወካዮች እንደሚታደሙ እየተጠበቀ ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Advertisement