“ማዕከላዊ አፍሪካ ውስጥ ሬሳ ለፕሮፖጋንዳ ጥቅም እየዋለ ነው”፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

                     

ማዕከላዊ አፍሪካ ወስጥ የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ድርጅቶች በመሥሪያ ቤቶቻቸው ደጃፍ ላይ ሬሳዎችን በማስቀመጥ ለፕሮፖጋንዳ ጥቀም እያዋሉት ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ወቀሰ።

“አንዳንድ ሰዎች ሰላማዊ ሰዎችን ገላችሁብናል በማለት ሬሳዎችን እያመጡ ደጃፎቻችን ላይ ያስቀምጣሉ” ሲሉ በማዕከላዊ አፍሪካ የድርጅቱ ቃል-አቀባይ የሆኑ ሰው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዕለተ ረቡዕ ነበር የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ሰዎች 17 ሬሳዎችን ባንጉይ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት መሥሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ያስቀመጡት።

ሟቾቹ በተባበሩት መንግሥታትና በታጣቂዎች መካከል በተደረገ ግጭት የሞቱ ናቸው በማለት ነው ተቃውሞ አሰሚዎቹ ሬሳዎቹን ይዘው የመጡት።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ግን ሬሳዎቹ ሰላም አስከባሪዎችንና የመንግሥት ወታደሮችን በማደን የሚገድሉ የታጠቁ ወንጀለኞች ናቸው።

“የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ መተኮስ ሲጀምሩ በተነሳ ግጭት የሞቱ ሰዎች ሬሳዎች እንደሆኑ እናውቃለን” ሲሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ቭላድሚር ሞንቴይሮ ተናግረዋል።

“አንዳንድ ሰዎች ሬሳዎችን ለፕሮፖጋንዳ ሲጠቀሙ በማየታችን እጅግ አዝነናል የምናወግዘው ተግባርም ነው” ሲሉ ቃል አቀባዩ ጨምረው አሳውቀዋል።

እሁድ ዕለት ነበር የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስካበሪ ኃይል ከባንጉይ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ተልእኮ የጀመረው።

ቭላድሚር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኃይሉ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢገጥመውም ተልእኮውን ከማሳካት ወደኋላ አይልም።

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በአውሮፓውያኑ 2013 ‘ሴሌካ’ የተባለው ሙስሊም ታጣቂ ቡድን ስልጣን ላይ ወጥቶ ክርስትያን የሚበዛባትን ሃገር ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ ነው ወደከፋ ግጭት የገባቸው።

ነፃነቷን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በ1960 ያገኘችውና በማዕድን ሃብት የተትረፈረፈችው ሃገር ማዕከላዊ አፍሪካ 2016 ላይ ምርጫ ብታከናውንም እስካሁን ሰላም ሊሰፍንባት አልቻለም።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement