የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የጅግጅጋ ጉብኝት ፋይዳ

                      

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጀመሪያው ይፋዊ የሥራ ጉዟቸው ምክትላቸው ደመቀ መኮንን እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳን በማስከተል ወደ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ አቅንተው ነበር።

ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት መፍታት ያስችል ዘንድ ወደ ጅግጅጋ እንዳቀኑ የተነገረላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቆይታቸው ከክልሉ ፐሬዚዳንት እና ከማሕበረሰቡ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

እንደ አዲስ መሪነታቸው በክክልሎቹ መካከል ለተፈጠሩ ግጭቶች መፍትሄ ያመጡ ይሆን ሲል የሕብረተሰቡ አባላት ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ቢቢሲ ሶማልኛ ዘግቧል

“እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ መብቶቻችን እንዲከበሩልን ዘንድም አንጠይቃለን፤ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ድረስ” በማለት የሕብረተሰቡ አባላት ጥያቄ እንዳነሱም ተዘግቧል።

አልፎም ነዋሪዎቹ ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግን የሚመሰርቱ አራቱ ፓርቲዎች ያላቸው የውሳኔ ሰጭነት ኃይል ለሶማሊ ክልልም ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ለማስመለስ ቃል ገብተዋል።

“ለሰላምና ለአብሮነት በሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሥራዎች ውስጥ በቀደምትነት እንደምሳተፍ ፊት ለፊታችሁ ቃል እገባለሁ። ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የሶማሌ ወንድሞቻችን በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።” በማለት አቶ ለማ መገርሳ ገልፀዋል።

ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎችን አናግሮ የዘገበው ቢቢሲ ሶማልኛ ከሁለቱም ወገን ወደቀያቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሶ ተመሳሳይ ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱ የሚሰጉ ሰዎች መመለሰ አንሻም እያሉም መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

በጅግጅጋ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ የነበረው ኬረዲን ከድር በአሁኑ ወቅት በአማራሴ ተፋናቃዮች ጣቢያ ተጠልሎ ይገኛል። በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የጅግጅጋ ጉብኝት የተሰማውን ደስታ የሚገልፀው ኬረዲን “ሰላም ለአንድ ሃገር መሠረት ነው” ይላል። ሆኖም ግን “ያለው ነገር እስኪፈታ ድረስ ለመመለስ ስጋት አለኝ፤ ምክንያቱም በግጭቱ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ሳስብ በጣም አስፈሪ ነው።” በማለት ያለውን ስጋት ገልጿል።

ከዚህ በፊት እንደሚታወሰው የሁለቱ ክልሎች በለሥልጣናት ግጭቱን ለመፍታት ቃል ገብተው ነበር። የአሁኑን ውይይት ግን ለየት እንደሚያደርገው የፖለቲካ ተንታኙ ገረሱ ቱፋ ይገልፃል።

“በትክክልም ግጭቱ ተፈቷል በተባለ በሰዓታት ልዩነት ዳግም ሲያገረሽ አስተውለናል። ይህ ተፈጥሯዊ ግጭት አይደለም፤ ማለትም በግጦሽ ወይም በመሰል ምክንያቶች የተከሰተ ግጭት አይደለም። ይህ የተቀናበረ ግጭት ነው ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ እንዲፈታ የማይፈልግ ኃይል መኖሩ እሙን ነው” ሲል ገረሱ ያስረዳል።

“ምናልባትም ይህን ጉብኝት ልዩ የሚያደርገው የኦሮሚያ አስተዳደሪ የነበረ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ መሄዱ ነው። ሙሉ ሥልጣን አለው ወይ? ሌላ ጥያቄ ሆኖ ሳለ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚያመጡትን ለውጥ ማየት ግን አጓጊ ነው” በማለት ገረሱ ይገልፃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀጣይ ወደ አምቦ እንዲሁም መቀሌ በመጓዝ ከነዋሪዎችና እና አስተዳዳሮዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዙ እየተዘገበ ይገኛል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement