ዶ/ር አብይ በግላቸው ለውጥ ያመጣሉ?

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ መረጋጋት እርቆት ከሰነበተ ቆይቷል። በዚህም የተነሳ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተስተውለዋል። ይህንን ተከትሎም ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ አድርጓል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

ነገር ግን ሕዝባዊ ተቃውሞዎች፣ በመንግሥት ኃይሎች የሚወሰዱ የኃይል እርምጃዎች እና እስሮች ቀጠሉ።

ይህ ደግሞ ግንባሩ በድጋሚ ለተሀድሶ እንዲቀመጥ አስገደደው። ያንንም ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን ልልቀቅ ሲሉ ጠየቁ። በርካታ የፖለቲካ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች ከእስር ተለቀቁ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ለሁለተኛ ጊዜ በድጋሚ ተደነገገ። ከዚህ ሁሉ በኋላ አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሦስተኛው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

በአሜሪካ ጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ገዳሙ የዶ/ር አብይ ቀጠዩ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ሆኖ መመረጥ ባለፉት ሳምንታት ኢህአዴግ ተከፋፍሏል እየተባለ ሲነገር ከነበረው አንፃር ካየነው፤ ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን ጠብቆ የወጣበትና ወደ አንድነት የተመለሰበትን መንገድን ማሳያ ነው ይላሉ።

ለዶ/ር ዮሐንስ ገዳሙ ኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅታዊ ባህል አለው። ሁሌም የጋራ ችግሮቹን በጣም ረጃጅም ጊዜ ወስዶ በመነጋገር ወደ አንድነት የሚመጣበትን ባህል አለው።

“ያንንም ያሳኩ ይመስለኛል። ስለዚህ የዶ/ር አብይ የፓርቲው ሊቀ-መንበር ሆኖ መመረጥ ትልቁ ድል ነው ብዬ የማስበው ለራሱ ለድርጅቱ ነው” ይላሉ።

አቶ ክቡር ገና ደግሞ በበኩላቸው የዶ/ር አብይ መመረጥ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ለውጥ ፈላጊው አካል የተሻለ ተደማጭነት አግኝቶ ማሸነፉን ያሳያል ባይ ናቸው።

የኢትዮጵን ፍላጎት

ዶ/ር ዮሐንስ ገዳሙ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን የሚያጠናክር፣ በሕዝቦች መካከል ትስስርን የሚፈጥር፣ ለወጣቶች፣ ለሴቶች አዲስ ተሰፋን ሰንቆ ሀገሪቱን በተረጋጋ ሁኔታ መምራት የሚችል መሪ ይፈልጋሉ ስለዚህ ለዜጎች የዶ/ር አቢይ መመረጥ እንደ አንድ ተስፋ ሰጪ እድል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ለዶ/ር ዮሐንስ ይህ ተስፋ ሰጪ ብቻ ሳይሆን በራሱ ተግዳሮቶችንም ያዘለ ነው።

የአራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲ አመራሮች ለ17 ቀን ከዘለቀው ስብሰባቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ ቃል የገቡትን ትልልቅ ማሻሻያዎች የተመረጠው አዲስ ሊቀመንበር እና ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያሳካ ይችላል ወይ ብቃትስ አለው? ብቃቱስ ቢኖረው ኢህአዴግ ፈቃደኛ ሆኖ ያሰራዋል? የሚሉት ጉዳዮችን በጥያቄ መልክ ያነሳሉ።

ዶ/ር ዮሐንስ የአዲሱ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር መመረጥ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ላለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊያስቆመው ይችላል ይላሉ።

ነገር ግን በአማራ ክልል የተነሳው ተቃውሞ ከማንነት ጥያቄ ጋር የተነሳ በመሆኑ ህዝቡ የሚፈልገውን በመረዳት ወደታች ወርዶ በማነጋገር መልስ መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ የፍትሃዊነት እና የእኩልነት ጥያቄ በመሆኑ እና ይህ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን አጠቃላይ ጥያቄ ስለሆነ ለዶ/ር ዮሐንስ በአንዴ የሚመለስ አይደለም።

ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ፍንጮችን በማሳየት የህዝቡን ትዕግስት መግዛት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ቀጣይ ኃላፊነቶች

አቶ ክቡር ገና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀዳሚ ሥራዎች ፓርቲው የሚያስቀምጣቸው ቢሆኑም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዘለቂ ሰላምን በማምጣት ረገድ ምን ያህል እንዳገዘ መመልከት እና ውሳኔ መስጠት ግን ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ዶ/ር ዮሐንስም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ኢህአዴግ በተደጋጋሚ የሚታወቀው ተሀድሶ በማካሄድ ነው። በቅርቡም ጥልቅ ተሃድሶ አካሄዷል። ወደ ተግባር ስንመጣ ግን ብዙ ጥያቄ የሚያስነሱ ነገሮችን ብዙ ጊዜ እናያለን ይላሉ ዶ/ር ዮሐንስ።

በቅርቡ ታዋቂ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች ከእስር መለቀቃቸውን የሚያስታውሱት ዶ/ር ዮሐንስ፤ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በእስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ ይናገራሉ።

በመቀጠልም በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም እነዚያን የተለቀቁ እስረኞችንና ሌሎችንም ወደ እስር ቤት የማስገባት ነገር በድጋሚ መታየቱን በማንሳት፤ የኢህአዴግን ጥልቅ ተሃድሶ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገቡታል።

ስለዚህ ዶ/ር ዮሐንስ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሀገሪቱ ትልቅ ስልጣን ስለሆነ ይህንን ዶ/ር አቢይ በርካቶችን ወደ እስር ቤት መልሶ ያስገባውን የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቀልበስ የመጀመሪያ ሥራቸው መሆን ብለው ያስባሉ።

አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል በማለት ያነሱት ለወጣቶች ሥራ መፍጠርንና ሙስናን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ዶ/ር ዮሐንስ ደግሞ ይህንን ለማድረግ ተቋማዊም ሆነ ፖለቲካዊ ለውጦችን ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።

እንደ ዶ/ር ዮሐንስ ከሆነ ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ እምነቱን በመከተል እስካሁን ድረስ ተጉዞ የትም ስላላደረሰው ዶ/ር አቢይ አዲስ የሆነ ሀገሪቱ የምትመራበት፣ ለህዝቡ ተስፋን የሚሰንቅ፣ አዲስ አመለካከት መቅረፅ ያስፈልጋቸዋል።

“ዶ/ር አቢይ ከተማረው ወገን በመሆናቸው እነዚህን ጉዳዮች ያስቡበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላሉ።

በተጨማሪም ሀገሪቱን ማረጋጋት፣ የምትመራበት ፌደራላዊ ሥርዓት ለብዙ ችግር የዳረጋት ከመሆኑ አንፃር እሱን ማስተካከልም ከሥራቸው መካከል እንደሚገኝበት ያስታውሳሉ።

“ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ስደተኛ ሆነዋል። ይህ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በማዕከላዊ መንግሥቱ የተወሰዱ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች አይታዩም። እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ ወይ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

በተጨማሪም ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችንና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናን የሚይዙበት መንገድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቃት መፈተኛዎች መሆናቸውንም ዶ/ር ዮሐንስ ያስረዳሉ።

የኢህአዴግ የፓርቲ ባህል

እንደ ዶ/ር ዮሐንስ አመለካከት ከሆነ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱበት ጊዜ አንስቶ በኢህአዴግ ውስጥ የቡድን አመራር የሚባል ነገር ገኖ ታይቷል።

ይህ ደግሞ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትርም ጠፍንጎ ይዞ ብዙ ሥራ እንዳይሰሩ ሊያደርጋቸው ይችላል ሲሉ ይሰጋሉ።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትርነት በሀገሪቱ ውስጥ ያለ ትልቁ የመንግሥት ሃላፊነት ስለሆነ የሚኖረውን ተግዳሮት በአጠቃላይ ተቋቁሞ መስራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

በፖለቲካዊ ተሳትፎ ውስጥ የማይታወቁ ምሁራንን በካቢኔያቸው ውስጥ እና ከዚያም ውጭ በማሳተፍ በጋራ መስራት ያስፈልጋል። ይህንንም ይላሉ ዶ/ር ዮሐንስ አዲሱ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራቸውን ሲጀምሩ በሚፈፅሙት ቃለ መሃላ እና በሚወስዷቸው እርምጃዎች የምናየው ይሆናል።

ከገዢው ፓርቲ የቆየ አሰራር አንፃር አቶ ክቡር ገና አዲሱ ሊቀ-መንበር ከተለመደው የኢህአዴግ የቡድን አመራር ባህል ይወጣሉ ብለው አያስቡም። ይህንን ለማለት ያበቃቸው ደግሞ ዶ/ር አብይ አህመድ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዷት የሚያሳይ ምንም የፃፉትም ሆነ የገለፁበት መድረክ ባለማየታቸው ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement