በርበራ አዲስ የባሕር በር ወይስ አዲስ ውዝግብ

                

ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ወደቡን ከሚያስተዳድረው የዱባዩ ዲ ፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር መጋራቷ ይታወቃል።

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለገቢ እና ወጪ ንግዷ ለመጠቀም የሚያስችላትን መሰረተ ልማት እንደምታለማ ተገልጿል።

በወቅቱም የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ተከታታይ ድርድርን ከሶማሌላንድ እና ከዲፒ ወርልድ ግሩፕ ጋር ካካሄደች በኋላ በበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ማግኘቷን ገልፀዋል።

ይህ ግን የሶማሊያን መንግሥት አላስደሰተም፤ የሶማሊያ ፓርላማ ሉአላዊነታችን ተነክቷል በማለት ስምምነቱን ውድቅ አድርጎታል። የሶማሌላንዱ ፓርላማ ግን ወዲያውኑ ስምምነቱን አፅድቆታል።

ይህ የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ ግን ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባለሙያው አቶ ዳደ ደስታ ውሃ የሚቋጥር ሀሳብ አይደለም። እንደ እርሳቸው ከሆነ ይህ ኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ያደረጉት ስምምነት ልክ እንደማንኛውም የንግድ ስምምነት ነው ይላሉ።

ሉአላዊነትን የሚጋፋ እንዲሁም ለሶማሌላንድ እውቅና የሚሰጥም አይደለም የሚሉት አቶ ዳደ፤ እርሳቸው ልክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሶማሊላንድ እንደሚያደርገው ጉዞ ነው የሚያዩት። “ይህ በባህር እና በየብስ ስለሆነ ይለያል ካላልን በስተቀር ምንም ችግር የለውም” ባይ ናቸው።

ፖለቲከኛውና በኢትዮጵያ ወደብ ባለቤትነት መብት ላይ የሚያተኩረው “አሰብ የማናት?” መፅሃፍ ደራሲ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ የገዛችው የ19 በመቶ ድርሻ የወደብ ችግርን በመጠኑም ቢሆን ፋታ ይሰጥ ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ብለው አያምኑም።

እንደ እርሳቸው ሃሳብ ከሆነ የወደብ ችግራችን ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችለው አሰብ ወደ ኢትዮጵያ እጅ ሲገባ ብቻ ነው።

እንደ ዶ/ር ያዕቆብ ከሆነ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ሶማሌላንድ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ናቸው። እነዚህ ሀገራት እርስ በእርስም ቅርበት አላቸው። እንዲሁም ጅቡቲ ከበርካታ ሀገራት ጋር ስትራቴጂካዊ ትስስርን ፈጥራለች።

“ወደቦቿን ቻይናዎች፣ እንግሊዞች፣ ፈረንሳዮች እና ግብፆች ይጠቀሙታል። ግብፅም ብትሆን ወታደራዊ ማዕከል በኤርትራ መስርታለች። ይህ ብቻ ሳይሆን ግብፅ በደቡብ ሱዳንም ወታደራዊ ማዕከል አላት” በማለት የስጋቱን ግዝፈት ለማሳየት ዶ/ር ያዕቆብ ይሞክራሉ።

ግብፅ በሶማሌላንድም የወታደራዊ ማዕከል ለመመስረት ስምምነት እያደረገች ነው ሲሉ በስጋቱ ላይ ሌላ ስጋት እንዳለ ያሳያሉ።

ስለዚህ ለዶ/ር ያዕቆብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኢትዮጵያ በአረብ ሀገራት ተከባለች ማለት ይቻላል። ስለዚህ እያንዳንዱ ውሳኔዋን ከጂኦፖለቲካዊ ጥቅም አንፃር መፈተሽ ተገቢ ነው።

አቶ ዳደም ይህ አካባቢ የተረጋጋ ባለመሆኑ እያንዳንዱ ሥራ እና የንግድ ልውውጥ ጂኦፖለቲካዊ ትርጉም እየተሰጠው እና ሌሎች ሀገራት ከዚህ ግንኙነት መፍረስ ለማትረፍ በዜሮ ድምር ስሌት ስለሚጓዙ ስምምነቶች እና እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ሊጤኑ ይገባል ይላሉ።

አቶ ዳደ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት የሶማሊያ መንግሥትን በማነሳሳት እና ሉአላዊነታችሁ ተደፈረ በማለት ተቃውሞ እንዲያሰሙ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ያምናሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከዚህ ወደብ ድርሻ መግዛቷ ስልታዊ ውሳኔ መሆኑን ያሰምሩበታል።

ዘላቂ መፍትሔ

ለዶ/ር ያዕቆብ ዘላቂው መፍትሄው ከኤርትራ ጋር ሰላም መስርቶ መደራደር ነው። ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር በ1952 በፌዴሬሽን ስትቀላቀል “የኢትዮጵያ ሕጋዊ የሆነ ወደ ባህር የመዝለቅ መብቷ እንዲጠበቅ ኤርትራ በፌዴሬሽን ተቀላቅላለች” ይላል የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ።

ለዶ/ር ያዕቆብ ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ የነበራትን መብት ያጣችው በኢህአዴግ ስህተት ስለሆነ የባህር በር የማግኘት መብታችን መረጋገጥ አለበት።

አክለውም የባህር በር ማጣት የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የህልውናም አደጋ እንዳለው አመልክተው፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ደህንነቷን ለማረጋገጥ ከኤርትራ ጋር ተደራድራ አሰብ ወደብ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋታል ይላሉ።

አቶ ዳደ ደግሞ ወደቦችን በማስተዳደር የተሰማሩ የአረብ ሀገራትን ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ልትመለከታቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ።

“እነዚህ ድርጅቶች ከፖለቲካ የጸዳ እንቅስቃሴ ይዘው መምጣታቸው እና አለመምጣታቸው በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። በዚህ አካባቢም ሆነ በአረብ ሀገራት የግብፅ ተፅእኖ ቀላል አይደለም” በማለት ከግብፅ ጋር ያለን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ያስታውሳሉ።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን የገቢ እና የወጪ እቃዎቿን ለማጓጓዝ በዋናነት ብትጠቀምበትም ሌሎች አማራጮች እንደሚያስፈልጓት እሙን ነው የሚሉት አቶ ዳደ “በርግጥ ወደፊትም የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያ ዋነኛ የወጪ እና የገቢ እቃዎች ማስተላለፊያ በር ሆኖ መቀጠሉ አይቅርም” ይላሉ።

                      

“ነገር ግን ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ብቻ ልትጠቀም አትችልም። የበርበራ ወደብ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ለሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢች ስትራቴጂካዊ ጥቅም አለው” ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

በዚህም የተነሳ ለአቶ ዳደ አማራጭ ወደብ በመፈለጋችን ምክንያት በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የሚፈጠር አለመግባባትም፤ ልክ እንደ እስከዛሬው ሁሉ በመነጋገር የሚፈታ እንደሆነ ያምናሉ። በወደብ አጠቃቀም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶች ወቅታዊ ሁኔታን የሚከተሉ በመሆናቸው ጥርስ የሚያናክስ እንደማይሆንም ያምናሉ።

በበርበራ ወደብ ላይ ከፍተኛውን የባለቤትነት ድርሻ ያዘው የዱባዩ ኩባንያ ቢሆንም የሶማሊያ ፓርላማ አባላት የቅሬታ ትኩረት ግን በኢትዮጵያ ተሳትፎ ላይ ነው። ይህም ሠራዊቱን አሰማርቶ ከአልሸባብ ጋር እየተፋለመ ያለውን የኢትዮጵያን መንግሥት ቅር ማሰኘቱ አይቀርም።

ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነትን 2008 ላይ ነው ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው። ሀገሪቱ 30 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግዷ በበርበራ ወደብ በኩል እንዲወጣ ብትፈልግም እስካሁን 97 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግዷ በጂቡቲ ወደብ በኩል ነው እየተካሄደ ያለው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement