”እኔ በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም” ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ

          

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ በቅርቡ በሀገር ውስጥ ለሚታተም አንድ ጋዜጣ ‘ግልፅ ደብዳቤ በሀገር ውስጥና በውጭ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን’ በሚል ዘለግ ያለ ደብዳቤ ፅፈው ነበር። ለዚህ ደግሞ ሰበብ የሆናቸው ሰዎች በተለያየ ምክንያት የጥላቻ ንግግር ሲናገሩ ማየታቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። ይህ አሳስቧቸውም ደብዳቤውን ለመፃፍ እንደተነሱ ይናገራሉ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ በተለያዩ ሃገራት በጥላቻ ንግግር ምክንያት በርካታ ነገር ተከስቷል። የሰው ልጅ ቢከባበር፣ ቢፈቃቀር፣ ባይግባባ እንኳን በክብር መከራከር ቢችል እና የጥላቻና የስድብ ቃል ቢያስወግድ ጥሩ ነው ይላሉ።

ደብዳቤያቸውን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደፃፉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር፤ ፖለቲከኛ ሆነ ቄስ ወይም ደግሞ ምዕመን ሁሉም ከጥላቻ ቃል ራሳቸውን አቅበው በመከባበር እና በመደማመጥ እንዲነጋገሩ ይመክራሉ።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይህንን ደብዳቤ ሲፅፉ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ነገር ተከናውኗል። ከሦስት ዓመታት በላይ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ዋጋ አስከፍሏል። በርካታ ፖለቲከኞች ለእስር ተዳርገዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ለሁለተኛ ጊዜ ተደንግጓል። ስለዚህም ይህንን ለማለት በጣም ዘግይተዋል የሚሉ ግለሰቦች አሉ።

ፕሮፌሰር ግን ”አልዘገየሁም” ይላሉ። ለዚህ አስረጅ ብለው የሚገልፁት ደግሞ በተለያየ መድረክ ላይ ስለመከባበር እና ስለመደማመጥ መፃፋቸውን፣ እድል አግኝተው ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙበት ጊዜ ሁሉ ይህንን ሀሳብ አንስተው መናገራቸውን እና የተቻላቸውን ነገር ማድረጋቸውን ነው።

ለፕሮፌሰር ይህ የጥላቻ መንፈስ የመጣው ከሰው ልጅ ባህሪ መሆኑን ያምናሉ። በቅዱስ መፃህፍትም ውስጥ የአቤል እና የቃየን ታሪክ የሚያሳየን ያንን መሆኑን ያስረዳሉ። ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን የመከባበርና የመፈቃቀር ባህላችን በጣም ጠንካራ ስለሆነ ከሌሎች ህዝቦች የተለየና የተሻለ መንፈስ አለን ብለውም ያምናሉ።

ቆይታ ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ጋር

ፕሮፌሰር በሀገሪቱ ውስጥ አሁን የተለያዩ ወገኖችን ለማሸማገል የሚሰሩ ጥረቶች እንዳሉ የተናገሩ ሲሆን፤ ይህ ጥረታቸው የተጀመረው የዛሬ ሰላሳ ዓመት እንደሆነ ያስታውሳሉ። በርግጥ በአሁኑ ሰዓት የሚካሄደው ድርድር ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመናገር ”በአንድ እግር ቆሞ” እንደመናገር እንደሚሆንባቸው የጠቀሱ ሲሆን ነገር ግን ሌት ተቀን ከእንቅልፋቸው ተፋተው ስለሀገራቸው ሰላም እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ ወገኖች ፕሮፌሰር ኤፍሬምና የሽምግልና ቡድኑ ወደ ዕርቅ መድረኩ የሚመጡት ችግሮች ተባብሰው መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ እንደሆነ ይናገራሉ። ፕሮፌሰሩ ግን በዚህ አይስማሙም።

ዘወትር ለኢትዮጵያ ሰላም ከመንግሥት ወገን ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ለምሳሌም እንደ ኦነግ እና ግንቦት 7 ካሉ የፖለቲካ አካላት ጋር ሁሉ እንደሚነጋገሩ ይጠቅሳሉ።

ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ደብዳቤ ተፅፎ ተሰጥቷቸው ለመንግሥት አድርሰው የታሰሩ የትግል አጋሮቻቸው እንዲፈቱ ጥረት እንዳደረጉም ያስታወሳሉ።

ስለዚህ ሁሌም የሰላም ሥራ ያለማቋረጥ እንደሚከናወን የሚያወሱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ለእርሳቸውም ሆነ አብረዋቸው ለሚሰሩ ግለሰቦች ”የሰላም ጥረት የወሬና የስብከት ጉዳይ እንዲሁም የአደባባይ ሥራ አይደለም” ብለው በይፋ እየተነገረ እንደማይሰራ ይገልፃሉ።

”ሰላም በክብር እና በፍቅር ከሚመለከተው ሰው ጋር፣ ከወዳጅም ሆነ ከጠላትም ጋር ቢሆን መነጋገርና መመካከርን ይጠይቃል” ሲሉ ያክላሉ።

ማንኛውም ሰው እስር ቤት ገብቶ ሲንገላታ ዝም ብለን አናውቅም የሚሉት ፕሮፌሰር ችግር ሲኖር ብቻ ሳይሆን፤ ችግርም በሌለበት ጊዜ ሰላም ላይ እየሰራን ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

አሁን ሀገሪቱ ስለገባችበት ውጥንቅጥ፣ ስለሞቱ ሰዎች፣ በእስር ስለተንገላቱና ቤተሰባቸው ስለተበተነ፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ስለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ልባቸው በሀዘን እንደሚከብድ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መፍትሔው ግን በኢትዮጵያውያን እጅ እንደሆነ ያምናሉ።

”እኔ በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም” የሚሉት ፕሮፌሰሩ መንግሥትና ተቃዋሚ ኃይሎች አይናቸው እንዲከፈት እንደሚፀልዩ፣ የተቻላቸውንም አቤት እንደሚሉ እና ችግር ሁሉ በውይይት ይፈታል ብለው ስለሚያምኑ ሁሉም ወገኖች እንዲወያዩና እንዲነጋገሩ ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ የጥንት ሴማዊ ቋንቋዎችና ሥልጣኔዎች እንዲሁም የአፍሪካ/ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሃይማኖት ሊቅ ናቸው፡፡ በፕሪንስተን ኒው ጀርሲ የሴማዊ ጥናቶች ተቋም ዳይሬክተር እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ማዕከል የቦርድ አባልም ናቸው፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement