አሜሪካ 60 የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ልታባርር ነው

                  

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 60 የሩሲያ ዲፕሎማቶች አሜሪካን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ሩሲያ የቀድሞ ሰላይዋን በነርቭ ጋዝ መርዛዋለች የሚለውን ውንጀላ ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል።

ዋሽንግተን ከዲፕሎማቶቹ በተጨማሪም በሲያትል የሚገኘው የሩሲያ ቆንስላ ፅህፈት ቤትን ልትዘጋ ትችላለችም ነው የተባለው።

አሜሪካን ለቀው እንዲወጡ ከታዘዙት መካከል 48ቱ በዋሽንግተን የሩሲያ ኤምባሲ ሰራተኞች ናቸው።

ቀሪዎቹ ደግሞ በመንግስታቱ ድርጅት ዋናው መስሪያ ቤት የሩሲያ መልዕክተኛና ዲፕሎማት ናቸው ተብሏል።

ጀርመን ፣ ፈረንሳይ እና ዩክሬንም በተመሳሳይ መልኩ የሩሲያ ዲፕሎማቶች ሃገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሸንኮ 13 የሩሲያ ዲፕሎማቶች ሃገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን ገልጸዋል። 

በዛሬው እለትም ላቲቪያ፣ ሉቴኒያ፣ ኢስቶኒያ እና ፖላንድ በሃገራቸው የሚገኙ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ለጥያቄ መጥራታቸው ተሰምቷል።

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ባለፈው ሳምንት በነበራቸው ስብሰባ፥ ሞስኮ ከቀድሞው ሰላይ መመረዝ ጀርባ እጇ አለበት በሚል መስማማማታቸው ይታወሳል።

ሩሲያ ከልጁ ጋር በእንግሊዝ የሚኖረውን የቀድሞ ሰላይ ሰርጌ ስክሪፓልና ልጁን በነርቭ ጋዝ መርዛለች በሚል ከበርካታ ሃገራት ውንጀላ ቀርቦባታል።

ይህን ተከትሎም በርካታ ሃገራት የሩሲያ ዲፕሎማቶች ሃገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እያስተላለፉ ነው።

ሩሲያ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የቀረበባትን ውንጀላ ያስተባበለች ሲሆን፥ እርምጃውን ለወሰዱ ሃገራትም አፀፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ ይጠበቃል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement