ስለ ቀዝቃዛ ምግቦች አንዳንድ ነጥቦች

                              

በመስከረም አያሌው

ብዙዎቻችን ወቅታዊውን የአየር ሁኔታ ለመቋቋም ከምናደርጋቸው ነገሮች መካከል ከወቅቱ የሙቀት መጠን ጋር ተቃራኒ የሆኑ ምግቦችንና መጠጦችን መጠቀም ነው። እንዲህ እንደ አሁን ቀዝቃዛ አየር በሚሆንበት ወቅት ሞቃታማ እና ለሰውነት ሙቀትን የሚሰጡ ምግቦችንና ትኩስ መጠጦችን መጠጣትን እናዘወትራለን። በተቃራኒው የአየሩ ሁኔታ ሞቃታማ በሚሆንበት ወቅት ቀዝቃዛ ምግቦች እና መጠጦች ተመራጭ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ አብዛኞቻችን በግምት የምናደርጋቸው ነገሮች በጤናችን ላይ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው ነው ባለሞያዎች የሚገልጹት። በተለይ ቀዝቃዛ ምግቦችና መጠጦች እንደምናስበው ሰውነታችንን ከማቀዝቀዝ አልፈው በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ በርካታ ጎጂ ተፅዕኖዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ ይላሉ ባለሞያዎች። እንደ አትክልትና የመሳሰሉትን ነገሮች በጥሬው መመገብ ጠቀሜታው ከፍተኛ ቢሆንም መመገብ ያለብን ግን ከሰውነታችን ሙቀት ጋር ተቀራራቢ የሙቀት መጠንን እንደያዙ መሆን አለበት።

ቀዝቃዛ ምግቦችን እና መጠጦችን ስናስብ በቅድሚያ ሊታሰብበት የሚገባው የምግብ መመረዝ ጉዳይ እንደሆነ ባለሞያዎች ያተኩሩበታል። ምግብ በሚቀዘቅዝበት ወቅት ለባክቴሪያዎች መራባት ምቹ ሁኔታዎች ስለሚፈጥሩ ምግቡ እንዲመረዝ እድል ይከፍትለታል። ምግቡ በቀዝቃዛው አገልግሎት ላይ ቢውልም ባክቴሪያውን ቀጥታ በመመገብ ለምግብ መመረዝ ችግር የመጋለጥ እድላችን ከፍተኛ ይሆናል። ከምግብ መመረዝ በተጨማሪም ቀዝቃዛ ምግቦችን መመገብ በርካታ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እንደሚያስከትል የሚያመለክተው ፅሁፍ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ታዋቂው የጤና እና ማህበረሰብ ጤና አሰልጣኝ ፕሮፌሰር ኒኮል ግራናቶ ቀዝቃዛ ምግቦች እና መጠጦች ከሚሰጧቸው ጠቀሜታዎች ይልቅ ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አስቀምጠዋል። ቀዝቃዛ ምግቦችና መጠጦች በተለይ የውጪው አየር ሞቃታማ በሚሆንበት ወቅት ቀዝቀዝ ለማለት በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ መሆናቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፤ የሰው ልጅ ከተለያዩ ወቅቶች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ሲል ከፈጠራቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ ይሄ እንደሆነ ገልጸዋል። ነገር ግን በሞቃታማውም ሆነ በቀዝቃዛው ወቅት ቀዝቃዛ ምግቦችን እና መጠጦችን ማዘውተር በጤናችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል ባይ ናቸው ፕሮፌሰሩ።

የሰው ልጅ የምግብ ልመት ሥርዓት ለሚወስዳቸው ምግቦች እና መጠጦች ቅርብ ስሜት ያለው ሥርዓት ነው። በተለይ ደግሞ የምንወሰዳቸው ምግቦች ያላቸው የሙቀት መጠን በጣም አስፈላጊው እና ወሳኙ ነው ይላሉ ባለሙያው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የቀዝቃዛ ምግቦች እና መጠጦችን ያህል የሰውን ልጅ ሥርዓተ ልመት የሚያዛባ ነገር እንደሌለ ተገልጿል። በተለይ እነዚህ ቀዝቃዛ ምግቦች እና መጠጦች ጠዋት ላይ ወይም በባዶ ሆድ በሚወሰዱበት ወቅት መላውን ሰውነት የማናጋት አቅም አላቸው። በዚህም የተነሳ በሰውነታችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሆርሞን አለመመጣጠን ያመጣል። ይሄም በቀጥታ የአንጎልን እንቅስቃሴዎች የመቀያይር እንዲሁም የተረፈ ምርት አወጋገድን (metabolism) የማዛባት አቅም ይኖረዋል። በእነዚህ አሉታዊ ተፅዕኖዎች የተነሳም አንጀት መደበኛ ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን ያደርገዋል።

ሌላው ቀዝቃዛ ምግቦችና መጠጦችን ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳት የምግብ ንጥረ ነገር ጉዳይ ነው። ቀዝቃዛ ምግቦችና መጠጦች ካላቸው የመቀዝቀዝ ባህሪይ የተነሳ በሰውነት ውስጥ ሲገቡ የሰውነት ህዋሳት ላይ የመጋገር እና የመዝጋት ባህሪይ ይኖራቸዋል። ይሄ ሲሆን ደግሞ ሰውነት ከተመገብነው  ምግብ ማግኘት ያለበትን የንጥረ ነገር መጠን ለመምጠት እና ወደ ውስጥ ለማስገባት እንዲቸገር ያደርገዋል። በመሆኑም የተመገብነው ምግብ ሆድን ከመሙላት በዘለለ ለሰውነት ግንባታ እና ለጤንነት የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮችን እንዳያገኝ ያደርገዋል ማለት ነው።

ሰውነታችን መደበኛ እና የተመቻቸ የምግብ ሥርዓተ ልመት እንዲኖረው እንዲሁም ከልመት በኋላ አላስፈላጊ የሆኑት ነገሮች በአግባቡ እንዲወገዱ፤ የምንመገበው ምግብ እና የምንወስደው ፈሳሽ ነገር የሙቀት መጠን ከሰውታችን የሙቀት መጠን ጋር ተቀራራቢነት ያለው መሆን ይገባል ይላሉ ባለሞያዎች። ምንም አይነት ምግብ ወይም መጠጥ ወደ ሆዳችን በሚገባበት ወቅት ሆዳችን ያንን ምግብ እና መጠጥ ለማላም የሚያገለግለውንና እንዛይም ያመነጫል። ኢንዛይሙ የሚኖረው የሙቀት መጠን ከሰውነት ሙቀት ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ቀዝቃዛ ነገርን በምንመገብበት ወቅት ኢንዛይም ቅዝቃዜውን ለመከላከል እና ልዩነቱን ለማጥፋት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ይገደዳል። በተጨማሪም እነዚህ ቀዝቃዛ ነገሮች የምግብ ቧንቧ ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ከሳንባ ከሚወጣው ሞቃታማ ፈሳሽ (ትነት) ጋር ይጋጫሉ። የእነዚህ ሁለት ተቃራኒ ሙቀቶች ግጭት ውጤት ደግሞ ሳንባ ውስጥ አላስፈላጊ የሆነ አክታ እንደፈጠር ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት የሳንባ የውስጠኛው ክፍል እንዲደፈን ስለሚያደርገው ኃይል እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በሳንባ ውስጥ እንደልብ መመላለስ እንዳይችሉ ያደርገዋል።

ምግብ ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ምግቡን በማላም እና ለሰውነት ለማድረስ ሰውነታችን ኃይል እና በቂ ሙቀት ያስፈልገዋል። እነዚህ ቀዝቃዛ ምግቦች ደግሞ ወደ ሆድ በሚገቡበት ወቅት በሆድ ውስጥ ያለው ሙቀት እንዲቀንስ ያደርጉታል። በመሆኑም በሆድ እቃ ውስጥ የሚከናወኑት ተግባራት አዝጋሚ እንዲሆኑ እና የተመገብነው ምግብም በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይፈጭ ያደርገዋል። ምግብ ሳይፈጭ በሆድ ውስጥ ለረጅም ሰዓት በሚቆይበት ጊዜ ደግሞ ባክቴሪያ ለመራባት የሚያግዘውን ሰፊ ጊዜ እንዲወስድ ያግዘዋል። እነዚህ ባክቴሪያዎችም ሆድ እቃ ተጨማሪ ጋዝ እንዲያመነጭ እና ሆዳችን እንዲያብጥ (እንዲነፋ) ያደርገዋል።

ቀዝቃዛ ምግቦችን እና መጠጦችን መጠቀም ጉዳቱ ከዚህ በተጨማሪም በአንጀት ግድግዳ ላይ የመርጋት እና መለደፍ ባህሪይ አላቸው። የመርጋት ችግሩ የተከሰተው በትልቁ አንጀት ላይ ከሆነ ከምግብ ተጣርተው የወጡ አላስፈላጊ ነገሮችን ለማስወገድ አቅም ስለማያገኝ የሆድ ድርቀትን ያስከትላል። ችግሩ የተከሰተው በትንሹ አንጀት ግድግዳ ላይ ከሆነ ደግሞ ተደጋጋሚ እና ከፍተኛ ድምጽ ያለው ግሳት እንዲከሰት ያደርጋል። በተጨማሪም ሰውነታችን ከምግቡና ከመጠጡ ጋር የገባውን ቅዝቃዜ ሊመቋቋም እና ለማመጣጠን በሚያደርገው ጥረት ሰውነት ከፍተኛ ለሆነ የውሃ እጥረት ይዳረጋል። የሽንት ባንቧም ቀጥታ ከትንሹ አንጀት ፊት ለፊት የሚገኝ በመሆኑ ትንሹ አንጀት ለቅዝቃዜ ሲጋለጥ በባንቧው ውስጥ ያለው ሽንት እንዲቀዘቅዝ ስለሚያደርገው ሽንትን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት እንዲቸገር ያደርገዋል። በዚህም ሳቢያ ሽንት ለመቋጠር መቸገር እንዲሁም ቶሎ ቶሎ ለመሽናት መገደድን ያመጣል።

ቀዝቃዛ ምግቦችን ቀጥታ መመገብ በተለየ ሆኔታ በሴቶች ላይ የሚያስከትላቸው በርካታ ጉዳዮችም አሉ። የመጀመሪያው ጉዳትም የምግቦቹ ቅዝቃዜ የወር አበባ ሂደት የተዛባ እንዲሆን እንዲሁም የእንቁላል መመረት ሂደትን ስለሚያዛባው በመራባት ሂደት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቆዳ ላይ የመቆጣት ስሜት፣ የፀጉር መሣሣት እንዲሁም ሽፍታዎች በሰውነት፣ በፊት እና አንገት በስፋት እንዲሰራጩ ያደርጋል። በሆድ ዕቃ ውስጥም ከመጠን በላይ የሆነ አሲድ እንዲመነጭ ቀዝቃዛ ምግቦችን በተከታታይ እና ለረጅም ጊዜ መጠቀም ስር የሰደዱ በርካታ ጉዳቶችንም ሊያስከትል ይችላል። ከእነዚህ መካከልም ጉንፋን፣ የቆዳ ድርቀት፣ የጉሮሮ ህመም እና የቶንሲል መጎዳትም ሊያስከትል ይችላል።

Advertisement