ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የደስታ መግለጫ ላኩ

                     

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ከሁለት ቀን በፊት በሩሲያ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላሸነፉት ቭላድሚር ፑቲን የደስታ መግለጫ ላኩ።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ባስተላለፉት መልእከት፥ የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖው በመመረጥዎ እንኳን ደስ አልዎት ብለዋል።

ለፕሬዚዳንት ፑቲንም መልካም ጤንነትን ለሩሲያ እድገትና ብልጽግናን መመኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ አያይዘውም፥ “በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀጣይ የአስተዳደር ዘመንም በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 120 ዓመታትን አስቆጥሯል።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች መፈራረማቸውም ይታወሳል።

በትምህርት ዘርፍም በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረትና ሩሲያ እስካሁን 13 ሺህ ኢትዮጵያውያን መማራቸውም ይነገራል።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ባሳለፍነው ወር ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ከጠቅላይ

ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም ሁለቱ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን በማሳደግ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል።

በተጨማሪም ለሰላማዊ ግልጋሎት የሚውል የኒውክሌር ሀይልን በጋራ ለማልማት ሀገራቱ ተስማምተዋል።

እንዲሁም ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ162 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የእዳ ስረዛ ማድረጓም ይታወሳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement