ስደተኞችን የታደገች የስፔን የእርዳታ መርከብ በቁጥጥር ሥር ዋለች

                

 

በሊቢያ የውቅያኖስ ዳርቻ የነበሩ 216 ስደተኞችን ወደ ጣልያን ይዛ የመጣች የስፔን የእርዳታ መርከብ በጣልያን ባለስልጣናት ቁጥጥር ሥር ውላለች።

‘ፐሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ’ የተሰኘችው የስፔን የእርዳታ መርከብ ሰራተኞች ስደተኞቹን ከጫኑ በኋላ ለሊቢያ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች አናስረክብም በማለት ወደ ጣልያን ይዘዋቸው መጥተዋል።

በጣልያኗ ፖዛሎ የወደብ ከተማ ከደረሰች በኋላ ነው የጣልያን ባለስልጣናት መርከቧ ቁጥጥር እንድትውል ትዕዛዝ ያወጡት።

የመርከቧ ሠራተኞች በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ጉዳዩ ውቅያኖስ ላይ የነብስ አድን በሚሰሩ ሰብዓዊ ድርጅቶችና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ውጥረት እንደሚያሳይም እየተነገረ ነው።

ሁኔታው የተከሰተው ያሳልፈነው ሃሙስ ሲሆን መርከቧ ከሊቢያ ወደብ 117 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ በመገኘት የእርዳታ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ላይ ሳለች የጣልያን አቻቸው ደውለው ሁኔታው በሊቢያዎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን ያሳውቃሉ።

ነገር ግን የስፔን እርዳታ መርከብ ሠራተኞች ስደተኞችን ጭና መሃል ውቅያኖስ ላይ የቆመች መርከብ ይመለከታሉ፤ የሊቢያ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ስደተኞችን ይዘው ሊመልሷቸው እንደሆነም ይረዳሉ።

ይሄኔ ነው በፍጥነት ስደተኞችን ወደ ጫነችው መርከብ በመጓዝ ስደተኞቹን ወደራሳቸው መርከብ መጫን የጀመሩት። ይህ ከሆነ በኋላ መርከቧ ለሁለት ቀናት ያህል ስደተኞችን የምታራግፈበት ወደብ ፍለጋ የአውሮፓን ሃገራት ታዳርሳለች።

አርብ ዕለት ከስደተኞቹ መካከል አንድ ነብሰ ጡር በመገላገሏ እሳንና ጨቅላውን በመያዝ ወደ ማልታ ይሄዳሉ። ከዚያም የቀሬትን 216 ስደተኞች በመያዝ ወደ ጣልያን ይመጣሉ።

ከዚህ ሁሉ ድራማ በኋላ ነው መርከቧ የእስር ትዕዛዝ የተቆረጠባት። የመርከቧ ሰራተኞች እንዲሁም የሰብዓዊ ድርጅቱ መስራቾችም በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ይደረጋል። ከሳሾቹ ጣልያኖች መርከቧ ዓለም አቀፋዊ ህግ ጥሰዋል ሲሉ ይከሳሉ።

ቢሆንም የተከሳሾቹ ጠበቃ “የሰው ሕይወት ማድን በሚል ክስ ሊቀጡን ፈልገው ይሆናል” ሲሉ ክሱን አጣጥለውታል።

ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ 600 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ጣልያን ተሻግረዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement