የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፅዕኖ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ

                            

ለሦስት ዓመታት ያህል የዘለቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ያለመረጋጋት፤ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት እና ለንብረትም መውደም ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር በአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ ጫና ስለማሳደሩ የመዋዕለ ነዋይ ባለሞያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

ያለመረጋጋቱን ተከትሎ ከአንድ ወር ገደማ በፊት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተለያዩ የምጣኔ ኃብት ዘርፎችን እንቅስቃሴ ሊያስተጓጉል እንደሚችል ስጋታቸውን የሚገልፁም አሉ።

የፀጥታ መደፍረስ ከሚያውካቸው ዘርፎች ቱሪዝም በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አዋጁ ዘርፉን ይጎዳዋል ብሎ እንደማያምን ይገልፃል። ያነጋጋርናቸው እንዳንድ የዘርፉ አባላት ግን በሥራቸው ላይ ጫና እንደሚኖረው ስጋት አላቸው።

በጎንደር ከተማ በውጭ አገር ጎብኚዎች የሚዘወተር አንድ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ እንደሚሉት ከሆነ በአማራ ክልል አሁን ያለው የፖለቲካዊ መረጋጋት መልካም አጋጣሚ ቢሆንም፤ አዋጁ ሥራቸው ላይ ደንቃራ እንደማይፈጥር መተማመኛ የላቸውም።

ስጋታቸውንም የሚያጠናከር ማስረጃ ሲጠቅሱም ገና ከአሁኑ ወደሃያ የሚጠጉ አባላት ያሉት የጎብኝዎች ቡድን አስቀድሞ የተያዘ ጉዞውን መሰረዙን በምሳሌነት ያነሳሉ። “አሁን ላይ የቱሪዝም ፍሰት እንደቀድሞው አይደለም፤ እጅጉንም ቀንሷል” ይላሉ።

“በተለይ ደግሞ ኤምባሲዎች የሚያወጡትን የማስጠንቀቂያ አዋጅ ተከትሎ ጎብኝዎች ተዘዋውሮ ለመጎብኘት የነበራቸውን ዕቅድ ይሰርዛሉ” ይሉናል።

በማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሠማሩት አቶ ብስራት አክሊሉ እንደሚስማሙትም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በበለጠ ጎብኚዎች የሚመጡባቸው አገራት የሚያወጧቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች ተፅዕኖ ያሳድሩበታል።

“ምንም እንኳ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ የሚባለው ላሊበላ በአዋጁ መደንገግ ምክንያት የቱሪዝም ፍሰቱ ይህን ያህል ባይጎዳም ሐረር ላይ ግን ተፅዕኖው የጎላ ነበር” ይላሉ ባለሙያው። አክለውም “በመጀመሪያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትልቁ ችግር የነበረው ዋስትና ሰጭ መሥሪያ ቤቶች ዋስትና አንሰጥም ማለታቸው ነበር። ይህም ፍሰቱ እንዲቀንስ ትልቅ ድርሻ ነበረው” ይላሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት ዘርፉ ክፉኛ የተጎዳው በዋናነት የተለያዩ የአውሮፓ አገራት እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ ዜጎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ከማስጠንቀቃቸው ጋር ተያይዞ ነው።

የድንጋጌው መኖር በራሱ በተለይም ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የሚጓዙ ጎብኚዎችን የሚያስበረግግ ቢሆንም፤ የፀጥታ ሁኔታው የተረጋጋ ከሆነ ዘርፉ እምብዛም ላይጎዳ እንደሚችል አቶ ብስራት ይናገራሉ።

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገዛኸኝ አባተ እንደሚሉት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 264 ሺህ የሚሆኑ የውጭ ሃገራት ዜጎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፤ በተለይም በትልቁ የኦሮሚያ ክልል እና የበርካታ የጎብኚዎች መዳረሻ በሆነው የአማራ ክልል ግጭቶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች የነበሩ መሆናቸው በዘርፉ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ገዛኸኝ፤ መጠነኛ ተፅዕኖ መኖሩ አይቀርም ይላሉ።

በ2009 የነበረው የጎብኚዎች ፍሰት ከቀዳሚው ዓመት በ2.2 በመቶ ቀንሶ መገኘቱንም በአስረጅነት ያነሳሉ። የያዝነው የ2010 በጀት ዓመት የመንፈቀ ዓመት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ግን የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር መሻሻል ማሳየቱን አቶ ገዛኸኝ ይናገራሉ።

ከአንድ ወር በፊት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዘርፉ ላይ ያን ያህል ጫና ያሳድራል ብለው እንደማያምኑ የሚገልፁት ዳይሬክተሩ በምክንያትነትም አዋጁ መረጋጋትን የሚመልስና መሆኑን በአንድ በኩል፤ ጎብኚዎች በብዛት የሚመጡበት ዋነኛ ወቅት ማለፉን ደግሞ በሌላ በኩል ያነሳሉ።

አንድ የውጭ አገር ጎብኚ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሳልፈው አማካይ የቆይታ ጊዜ 16 ቀናት መሆኑን፤ ከሦስት ዓመት በፊት በተከናወነ ጥናት ማወቅ እንደተቻለም ኃላፊው ይገልፃሉ። አንድ ጎብኚ በቆይታው በአማካይ ከ234 በላይ ዶላር ያወጣል ተብሎ እንደሚገመትም ጨምረው ያስረዳሉ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement